ጆዜ ሞሪንሆ ከፌነርባቼ አሰልጣኝነታቸው ተሰናበቱ
ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ በቱርኩ ክለብ አንድ ዓመት ብቻ ቆይተው ተለያይተዋል፡፡ ውጤታማው አሰልጣኝ ፌነርባቼ በቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ በቤኔፊካ ተሸንፈው ከውድድር መውጣታቸው ለስንብታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡
ጆዜ በአሰልጣኝነት ቆይታቸው ከቶተንሃም ቀጥሎ ዋንጫ ሳያነሱ የለቀቁት ሁለተኛው ክለብ ሆኗል፡፡ የ62 ዓመቱ አንጋፋ አሰልጣኝ በ25 ዓመታት የአሰልጣኝነት ቆይታቸው 10 ክለቦችን መምራት ችለዋል፡፡ በቼልሲ በሁለት የተለያዩ ጊዜያት የቆዩባቸው አምስት አመታት በአሰልጣኝነታቸው ረጅሙን ጊዜ ያሳለፉበት ነው፡፡
ፌነርባቼ ደግሞ አንድ ዓመት ብቻ በመቆየት አጭር ቆይታ ያስመዘገቡበት ክለብ ሆኗል፡፡ ኢንተር ሚላን ፣ ሪያል ማድሪድ ፣ ማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲን የመሳሰሉ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦችን ያሰለጠኑት ፖርቹጋላዊ 26 ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችለዋል፡፡
የተፈላጊነታቸው መጠን እየቀነሰ የመጣው አሰልጣኙ በቀጣይ ወደ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ