ኢትዮ ቴሌኮም አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለሙዳይ የበጎ አድራጎት ማህበር 2 ሚሊየን 625 ሺህ ብር እና የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮ ቴሌኮም አመራሮች እና ሰራተኞች አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ የበጎ አድራጎት ተግባራት ማከናወን መርሐ ግብር አካሂዷል።
በዚህም በዋናው መስሪያ ቤት ደም ልገሳ የተከናወነ ሲሆን፣ በተጨማሪም ተቋሙ ለሙዳይ የበጎ አድራጎት ማህበር 2 ሚሊየን 625 ሺህ ብር እና የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ መልካም ስራ ማድረግ እና መከተል ትውልድን ለማሻገር ያግዛል ብለዋል።
አዲሱን ዓመት የምንቀበለው “ቀጣዩ አድማስ” በሚል ሰውን ማዕከል ባደረገ የሶስት ዓመት ስትራቴጂ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፣ በጎ ስራ ማከናወንም የተቋሙ ስትራቴጂ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢኮኖሚውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ኢንሼቲቮችን ቀርጾ ውጤታማ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በመላ ሀገሪቱ በርካታ ስራዎችን ከሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋርም በጋራ ለመስራት በጀት መመደቡን ጠቁመዋል፡፡
በዛሬው እለትም 960 ሺህ ደብተር ድጋፍ መደረጉን ገልፀው፣ ድጋፉ 80 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚደርግ ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ እስከ አሁን 3.2 ሚሊየን ደብተር ድጋፍ ማድረጉንም የገለጹ ሲሆን፣ በቀጣይም ይህንን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመሀመድኑር አሊ