በሴቶች ማራቶን በትዕግስት አሰፋ የብር ሜዳልያ ፤ በ10 ሺ ሜትር ደግሞ በጉዳፍ ፀጋይ የነሃስ ሜዳልያ ያገኘችው ኢትዮጵያ ዛሬም ተጨማሪ ሜዳልያዎችን ትጠብቃለች።
በወንዶች 10 ሺ ሜትር ውድድር ቅድምያ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል።
በውድድሩ እነማን ይሳተፋሉ?
ሰለሞን ባረጋ ሰለሞን ባረጋ በበርካታ ታላላቅ መድረኮች ላይ ሀገሩን ወክሏል። ትልቁ ስኬቱ በቶክዮ ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር ያስገኘው የወርቅ ሜዳልያ ነው። በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ5ሺ ሜትር የብር በ10ሺ ደግሞ የነሃስ ባለቤት መሆን ችሏል።
ሀገሩን በወከለባቸው የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮችም በ3ሺ ሜትር የወርቅ ፣ የብር እና የነሃስ በአጠቃላይ ሦስት ሜዳልያዎችን አስገኝቷል።
ዮሚፍ ቀጀልቻ ገና በወጣትነቱ ሀገሩን በተለያዩ ውድድሮች የወከለው ዮሚፍ ትልቁ ስኬቱ በዶሃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ ማግኘቱ ነው።
በቤት ውስጥ ውድድርም ሁለት ወርቅ ማምጣት ችሏል። የ28 ዓመቱ አትሌት በወጣቶች ውድድር ላይም ሜዳልያዎችን በማስገኘት ትልቅ አቅም እንዳለው አሳይቷል።
በሪሁ አረጋዊ የ24 ዓመቱ አትሌት ለሀገሩ ያስገኘው ትልቁ ስኬት ከዓመት በፊት በተደረገው የፓሪስ ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር ያመጣው የብር ሜዳልያ ነው።
የበለጠ የውድድር ልምድ ያገኘው አትሌቱ ዛሬ በሚደረገው የቶክዮ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወንዶች 10ሺ ሜትር የአሸናፊነት ግምት ካገኙ አትሌቶች አንዱ ሆኗል። ተጠባቂው ውድድር ቀን 9:30 ላይ ይጀምራል።
በሸዋንግዛው ግርማ