70ኛው የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዛሬ ይጀምራል

You are currently viewing 70ኛው የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዛሬ ይጀምራል

AMN-መስከረም 06/2018 ዓ.ም

በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ተከታታይ እያገኘ የመጣው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የ2025/26 የውድድር ዓመቱን ዛሬ ይጀምራል።

ምሽት 1:45 አርሰናል ወደ ሳንማሜስ ስታዲየም አቅንቶ ከአትሌቲክ ቢልባኦ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል። የባለፈው የውድድር ዓመት የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚው አርሰናል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አትሌቲክ ቢልባኦን ይገጥማል። በሀምሌ ወር በኤምሬትስ ካፕ የተጫወቱት ሁለቱ ክለቦች በፉክክር ጨዋታ ተገናኝተው አያውቁም።

አርሰናል አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድን በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ አድርጓል። ቡካዮ ሳካ እና ካይ ሃቨርትዝ ከጉዳታቸው አላገገሙም። ፈረንሳዊው ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ ግን ወደ ልምምድ ተመልሷል።

መድፈኞቹ ከስፔን ክለቦች ጋር ያላቸው ክብረወሰን ጥሩ የሚባል ነው። የባለፈው ዓመት የሪያል ማድሪድን የደርሶ መልስ ድል ጨምሮ ከስፔን ክለቦች ጋር ያደረጓቸውን አምስት ተከታታይ ጨዋታ አሸንፈዋል። የሚካኤል አርቴታ ስብስብ ዛሬ ካሸነፈ የስፔን ክለቦችን በስድስት ተከታታይ ጨዋታ ያሸነፈ የመጀመሪያው ክለብ ይሆናል።

ለሰሜን ለንደኑ ክለብ የዛሬው ጨዋታ ቀላል ይሆናል ተብሎ ግን አይጠበቅም። በሜዳቸው ኤስታዲዮ ሳንማሜስ ሞቅ ባለ ድጋፋቸው በሚታወቁት ደጋፊዎቹ የሚታጀበው ቢልባኦ በአውሮፓ ውድድሮች ካደረጋቸው የመጨረሻ 18 የሳንማሜስ ጨዋታ 14ቱን በድል ተወጥቷል።

ኮከቡን ኒኮ ዊሊያምስን በጉዳት የማያሰልፈው አትሌቲክ ቢልባኦ በቻምፒየንስ ሊግ ሲሳተፍ ከ10 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የሁለቱ ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 1:45 የሚጀምር ይሆናል። በሌሎች ጨዋታዎች ምሽት 1:45 ፒ ኤስ ቪ አይንዶቨን ከ ኡኑዮን ሴንት ጂልዋስ ይጫወታሉ። ምሽት 4 ሰዓት ላይ ደግሞ አራት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ይከናወናሉ።

ሪያል ማድሪድ በሜዳው ሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ኦሊምፒክ ደ ማርሴይን ሲያስተናግድ ጁድ ቤሊንግሃምን ከጉዳት መልስ ያገኛል። ቶተንሃም በሜዳው ቪያሪያልን ሲገጥም ፣ ጁቬንቱስ እና ቦሩሲያ ዶርትመንድ በአልያንዝ ስታዲየም ይጫወታሉ። ቤኒፊካ በሜዳው ስታዲዮ ዳሉዝ የአዘርባጂያኑን ካራባግ የሚያስተናግድበት ጨዋታም የዛሬ መርሃግብር አካል ነው።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review