ትራምፕ ከእርሳቸው በተቃራኒ የቆሙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፍቃድ ሊሰረዝ እንደሚችል ተናገሩ

You are currently viewing ትራምፕ ከእርሳቸው በተቃራኒ የቆሙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፍቃድ ሊሰረዝ እንደሚችል ተናገሩ

AMN – መስከረም 9/2018 ዓ.ም

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእርሳቸው በተቃራኒ የቆሙ ወይም የሚቃወሟቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ሊነጠቅ እንደሚችል ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ከ2003 ጀምሮ ከ20 አመታት በላይ በ ”ኤቢሲ” ሲሰራጭ የነበረው የጂሚ ኪምል “ሌት ናይት ሾው” በአሜሪካ ብሮድካስት ተቆጣጣሪ ተቋም መታገዱን ተከትሎ ነው።

ታዋቂው ኮሜዲያን ጂሚ ኪሚል በወግ አጥባቂው ተጽዕኖ ፈጣሪ ቻርሊ ከርክ ግድያ ዙሪያ በሰጠው አስተያየት ለአስርት አመታት ከሰራበት ቴሌቪዥን ጣቢያ በቋሚነት ታግዷል።

ጂሚ ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ የትራምፕ ደጋፊ እና “በግራ ዘመም ርዕዮተ አለም ተጠምቆ ያደገ ነው” ሲል ወንጅሏል።

በተጨማሪም ፕሮግራሙ ከመታገዱ በፊት በሰራው የመጨረሻ ፕሮግራም መግቢያ ላይ “ትራምፕ ከቻርሊ ከርክ ግድያ በኋላ ሀዘኑን የገለጸበት መንገድ አሳ እንደሞተበት የ4 አመት ህጻን ልጅ ያለ ነው” ሲል ተሳልቋል።

ከዚህ ባለፈም ትራምፕ እና አስተዳደራቸው የቻርሊን ግድያ የፖለቲካ ጥቅም ለማገኝት እየተጠቀሙበት ነው ሲል ወቅሷል።

ይህን ንግግር ተከትሎ ከፌዴራል ኮምኒኬሽን ኮሚሽን ማስጠንቀቂያ የደረሰው ኤቢሲ ስቱዲዮ ፈቃዱን በፍጥነት መሰረዙ በነጻነት የመናገር መብትን የተጋፋ ነው በሚል ተተችቷል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትላንትናው ዕለት ከብሪታንያ ጉብኝታቸው ሲመለሱ በኤርፎርስ ዋን ላይ በሰጡት መግለጫ፤ 97 በመቶ የሚሆኑት የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣብያዎች በምርጫ ዘመቻው ወቅት ከእርሳቸው ተቃራኒ እንደነበሩ መስማታቸውን ተናግረዋል።

“ብዙዎቹ ወይም 97 በመቶ የሚሆኑት ስለእኔ መጥፎ ነገር ብቻ ነበር የሚያወሩት ፤ ነገር ግን ምርጫውን በቀላሉ ማሸነፍ ችያለሁ። እነዚህ ጣብያዎች አሁንም ፈቃድ ይዘው መስራት እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም” ሲሉ ተናግረዋል ፕሬዝዳንቱ።

ግራ ዘመሙ ፖለቲከኛ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ቻርሊ ከርክ በህዝባዊ መድረክ ላይ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን ተከትሎ በቀኝ ዘመም እና ግራ ዘመም የአሜሪካ ፖለቲከኞች ዘንድ የፈጠረው ውጥረት መቀጠሉን ቢቢሲ ዘግቧል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review