ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የማገገሚያ ህክምና ማዕከል ግንባታ ተጀመረ

You are currently viewing ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የማገገሚያ ህክምና ማዕከል ግንባታ ተጀመረ
  • Post category:ጤና

AMN መስከረም 9/2018

ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የማገገሚያ ህክምና ማዕከል ግንባታ ዛሬ ተጀምሯል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ ጉዳት አገልግሎት ገፈርሳ ሳይት የሚገነባውን የተቀናጀ ማገገሚያ ህክምና ማዕከል ፕሮጀክት ግንባታን አስጀምረዋል፡፡ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የማገገሚያ ህክምና ማዕከል ግንባታው መጀመር መንግስት የጤና መሰረተ ልማትን ለማሟላት የጀመረውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የአካለ ድጋፍ አገልግሎት አማካኝነት የሚከናወነው ግንባታ በኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ወጪ የሚሸፈን ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው መሆኑን ተመላክቷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ የጤና መሰረተ ልማቶችን በማጠናከር የተሟላ የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የመከላከል እና አክሞ የማዳን አቅም እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የማገገሚያ ህክምና ማዕከል መገንባቱ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡ የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ የማገገሚያ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ ጉዳት አገልግሎት ገፈርሳ ሳይት የተጀመረው ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የማገገሚያ ህክምና ማዕከል ግንባታ በ17 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን በመግለጽ፤ በተያዘለት ጊዜ ዓለም አቀድ መስፈርቱን አሟልቶ ተገንብቶ ስራ እንዲጀምር ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታሪኩ ታደሰ በበኩላቸው ግንባታው ከዚህ በፊት የነበሩትን ውስን አገልግሎቶችን በስፋት ለማድረስ እንደሚያግዝ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከ23 ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች ዘመናዊና የተሟላ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review