በመዲናዋ የተሰሩ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማቶች ለመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ድምቀት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን የቱሪዝም ጋዜጠኛ የሆነው አስናቀ ብርሃኑ ገልጿል፡፡
በዓሉ ከሀገር ውስጥ ታዳሚዎች በተጨማሪ የውጪ ሀገር ጎብኝዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳር ልማቱ ተጨማሪ መስህብ በመሆን የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያረዝም ይሆናል ነው ያለው፡፡
አዲስ አበባ ቀደም ሲል የቱሪስቶች ማረፊያ እንጂ መደረሻ አልነበረችም ያለው ጋዜጠኛ አስናቀ፤ አሁን ላይ በመዲናዋ የተሰሩ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማቶች ማራኪና ሳቢ በመሆናቸው ከተማዋን ከቱሪስቱ ማረፊያነት ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ያደርጋታል ብሏል፡፡
ይህም መዲናዋ ከቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ ነው ሲል ተናግሯል ፡፡
በአደባባይ የሚከበሩ በዓላት የሀገሪቱን ባህል፣ እሴት እና መስህብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማቶች በተደማሪነት ለገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው፡፡
በመዲናዋ የተሰሩ የከተማ ውበት ሥራዎች ከሣቢነታቸው ባሻገር ከተማዋና ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚያወዳድራት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በአደባባይ በሚከበሩ በዓላት ላይ አለም አቀፍ ሚዲያዎች የዘገባ ሽፋን የሚሰጡበት በመሆኑ በመላው አለም የከተማዋን ብሎም የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ቀደም ሲል ቱሪስቶች ከመዲናዋ ውጪ ወደሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች ለመሄድ አዲስ አበባን እንደ መሸጋገሪያ እና ማረፊያ ይጠቀሙባት እንደነበር አስታውሷል፤
በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተደደሩ የወንዝ ዳር እና የኮሪደር ልማቶችን በመስራት የመዲናዋን መስህብነት ከፍ በማድረግ የቱሪስት የቆይታ ጊዜን ማራዘም አስችሏል ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜን በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲል ነው ጋዜጠኛ አስናቀ አስተያየቱን ያጋራን ፡፡
በ- በረከት ጌታቸው