AMN- መስከረም 19/2018 ዓ/ም
ምስጋና፣ እርቅ እና አንድነት የሚሰበክበት በዓል ኢሬቻ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ መከበር ከጀመረ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ ኢሬቻ ህብረብሄራዊ አንድነት ጎልቶ የሚታይበትና ማህበራዊ መስተጋብር የሚጎለብትበት የኦሮሞ ብሄር መገለጫ ነው።
የእርቅ፣ የምስጋናና የአንድነት ተምሳሌት በሆነው በዚህ የአከባበር ስን ስርዓር ላይ ቁርሾን ይዞ መታደም አይቻልም፡፡ በዚህም ምክንያት የተጣሉ ሰዎች በዓሉ የሚከበርበት ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ቀደም ብለው እርቅ ማውረድ ይጠበቅባቸዋል። የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ቦታ ላይ በንጹህ ልብ ምስጋና ይቀርባል፤ ምህረትም ይለመናል።
በኦሮሞ ብሄር ዘንድ የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን፤ የክረምት ወራት እንዳበቃ በሃይቅ ወይም በወንዝ ዳርቻ የሚከበርው ኢሬቻ መልካ እና በዓመቱ አጋማሽ የካቲት ወር ላይ በተራራማ ቦታ የሚከበረው ኢሬቻ ቱሉ መሆናቸውን ዩባ በየነ ሰንበቶ ለኤ.ኤም.ኤን ዲጅታል ተናግረዋል። ለኦሮሞ ሕዝብ ኢሬቻ መልካ የምስጋና በዓል ሲሆን፤ ኢሬቻ ቱሉ ደግሞ ፈጣሪ የሚለምንበት ነው።

ኢሬቻ ቱሉ የክረምቱ ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት ካልጣለ ድርቅ እንዳይከሰት ከወዲሁ በየካቲት ወር አጋማሽ አካባቢ ከፍ ባለ ተራራ ላይ በመውጣት ፈጣሪ የሚለመንበት ስርዓት ነው፡፡
በዚሁ ዕለት፤ ተራራውን የፈጠርክ ለእኛ ደግሞ ሰላምን ስጠን፣ ዝናቡን በወቅቱ አዝንብልን፣ ከጥፋት ጎርፍ ጠብቀን፣ አዝመራው ያማረ ፍሬ ያፍራ፣ ሀገሩ ሠላም ይሁን እያሉ በኢሬቻ ቱሉ ላይ ፈጣሪቸውን ይለምናሉ፡፡ በኦሮሞ ብሄር ዘንድ ኢሬቻ መልካ በተለየ ድምቀት የሚከበር ሲሆን በዓሉ ክረምቱ ተጠናቆ መስከረም ወር አጋማሽ አካባቢ ይከበራል፡፡
በክረምትና በወንዞች ሙላት ምክንያት ተራርቆ የከረመ ዘመድ አዝማድ ተገናኝቶ ደስታውን እና ናፍቆቱን እንዲሁም መልካም ምኞቱን የሚገልጽበት ነው። የበአሉ ታዳሚዎች ወደ ወንዝ ወይም ሐይቅ ዳርቻ እርጥብ ሣር ይዘው በመሄድ “መሬዎ….ሆ… ያ … መሬዎ …” በማለት ፈጣሪያቸውን በጋራ ያመሰግኑታል።
የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ በአስታራቂነታቸውና በሠላም አምባሳደርነታቸው የሚታወቁት ሃዳ ሲንቄዎች ከአባ ገዳዎች ፊት በመሄድ ወደ ኢሬቻ መልካ የሚደረገውን ጉዞ የሚመሩ መሆኑን ዩባ በየነ ሰንበቶ ይናገራሉ።

በዓሉ የሚከበረው በቱማሴራ ወይንም በጨፌ ድንጋጌ በተሰየሙ 6 መልካዎች መሆኑን የገለፁት ዩባ በየነ፤ ሆረ ሃርሰዲ፣ ሆረ ኪሎሌ፣ ሆረ ሀዶ፣ ሆረ ገንደብ፣ ሆራ ዋርጦ እና ሆረ ኤረር በተባሉ ሥፍራዎች የኢሬቻ መልካ በዓል በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች በድምቀት ይከበራል ነው ያሉት፡፡
በዋናነት በዓሉ የሚከበረው በቢሸፍቱ ከተማ በሚገኘው ሆረ-ሃርሰዲ እና በአዲስ አበባ ሆረ-ፊኒፊኔ ሲሆን፤በበዓሉ ላይ ሁሉም ባህላዊ አልባሳትን ለብሶ፣ የክት ያለውን ጌጣጌጥ አድርጎ እና ሌሎች ባህላዊ መገለጫ ቁሳቁሶችን ይዞ ለምስጋና ይታደማል፡፡
የአንድነትና የአብሮነት የሆነው ኢሬቻ መልካን ዘንድሮም ባህላዊ ቱፊቱን ጠብቆ መስከረም 24 በአዲስ አበባ/ፊንፊኔ/ ሆረ-ፊንፊኔ እንዲሁም መስከረም 25 በሆረ-ሀርሰዲ በቢሾፍቱ ይከበራል፡፡ ኢሬቻ ኢትዮጵያ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የገዳ ሥርዓት አካል መሆኑ ይታወቃል።
በ-በረከት ጌታቸው