የኑሮ ጫናን ለመቀነስ በተወሰደው ተከታታይ እርምጃዎች የኑሮ ውድነትን መቀነስ መቻሉን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አመላክተዋል፡፡
በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ሥነ- ሥርዓት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ፣ የኑሮ ጫናን እና የዋጋ ንረትን ለመቀነስ በተሰራው ሥራ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
በተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች በ2016 ዓ.ም ሰኔ ወር ከተመዘገበው 19 ነጥብ 9 በመቶ የዋጋ ንረት በ2017 ዓ.ም ተመሳሳይ ወር ላይ ወደ 13 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ብሎ መመዝገቡን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
መንግስት የመንግስት ሰራተኛውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ የደሞዝ ማሻሻያ ማድረጉን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ በዚህም ከዚህ በፊት ዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ 4 ሺህ 760 ከነበረበት ወደ ብር 6 ሺህ እንዲያድግ መደረጉን ገልጸዋል።
በወርቅነህ አቢዮ