የባህር በር ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች የዜጎችን ፍላጎት ያማከለና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ የሚያስችል ሆኖ እንዳገኙት ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃጸም እና በ2018 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም እንደ ሀገር የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ ድሎች፣ በተቋም ግንባታ እና በአገልግሎት አሰጣጥ የመጡ ለውጦች፣ ዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የፍትህና የህግ ሥርዓቱን ለማሻሻል የተከናወኑ አበይት ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት፣ የማዕድን ልማት አጠቃቀም እንዲሁም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ተፅዕኖ መፍጠር የመሳሰሉ ሀገራዊ ስኬቶች በፕሬዚዳንቱ ንግግር ተዳሰዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከልም ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላ ሀገራዊ የባህር በርን የተመለከተው ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሀሳብ ማድረግ መቻሉን አንስተው፣ የባህር በር ጥያቄ የቀጣናው የጋራ የመልማት ፍላጎትን ያገናዘበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ፕሬዚደንቱ በሁለቱ ምክር ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር ያለንበትን ወቅት የሚመጥን ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የባህር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች የዜጎችን ፍላጎት ያማከለ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ የሚያስችል ሆኖ እንዳገኙትም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አስናቁ ደምሴ፣ ቀደም ሲል በተፈጠሩ ስህተቶች ወደብ እየተከራየን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያሽቆለቁል የተደረገበት ሁኔታ ስለነበር፣ ይህን ጉዳይ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው አቢይ ርዕስ አድርገው ማንሳታቸው ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው ነዋሪ አቶ ደመቀ ጥላዬ፣ የባህር በር ከማግኘት ጋር ተያይዞ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መታገል እንደሚገባና የተነሳው ሳብም ቀደም ሲልም የነበረ ትልቅ የህዝብ ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል፡፡
መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዙ እቅዶችም እንዳስደሰቷቸው ያነሱት ነዋሪዎቹ፣ መንግስት ሀገራዊ ሰላም ለማረጋገጥ እየሄደበት ያለው ሂደትና ለወጣቶች የሰጠው ትኩረትም የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ በላይ ነጋሽ፣ የዲጂታል መታወቂያን ጨምሮ የተለያዩ የዲጂታል አሰራሮችን ጥቅም ላይ በመዋል አገልግሎትን ቀልጣፋ ለማድረግ ወደዚህ ዓይነት ዘመናዊ አሰራር ውስጥ መገባቱ የሚደገፍና ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ ፕሬዚዳንቱ ያነሷቸው ሀሳቦችን እና ዕቅዶችን ዳር ለማድረስ እንደ ዜጋ በጋራ መነሳት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
በታምራት ቢሻው