በሀሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ ደረሠኝ ሲገበያዩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች እና ደረሠኙን ያዘጋጀው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing በሀሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ ደረሠኝ ሲገበያዩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች እና ደረሠኙን ያዘጋጀው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN መስከረም 29/2018ዓ.ም

ሀሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ ደረሠኝ በመጠቀም ከሱፐር ማርኬት እንቁላል ሲገዙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች እና ደረሠኙን ያዘጋጀውን ግለሰብ በቁጥጥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ የማታለል ወንጀሉን ሲፈጽሙ በቁጥጥር ስር የዋሉት መስከረም 25 ቀን 2018 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረደ 7 ልዩ ቦታው ጃክሮስ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ሱፐር ማርኬት ውስጥ ነው።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ወደዚሁ ሱፐር ማርኬት ደምበኛ መስለው በመመላለስ እንቁላል ከ5 ሺህ እስከ 10ሺህ ብር በማዘዝ ሀሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ ሪሲት በመላክ ግብይት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

የሱፐር ማርኬቱ ሰራተኞች ምንም ገንዘብ ወደ አካውንታቸው ባለመግባቱ ባደረባቸው ጥርጣሬ ምክንያት ለድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ያሳወቁት ሲሆን በሱፐር ማርኬቱ ውስጥ በተገጠመ የደህንነት ካሜራ (CCTV) አማካኝነት ተጠርጣሪዎችን በመለየት በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለየረር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ጥቆማን ያደርሳሉ።

ፖሊስ በያዘው መረጃ ክትትል እያደረገ ባለበት ሁኔታ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች እንደለመዱት መስከረም 25 ቀን 2018 ዓ.ም በተመሳሳይ መልኩ ወንጀሉን ለመፈጸም ወደ ሱፐር ማርኬቱ ሲመጡ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ ሊያዙም ችለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተደረገ ምርመራ ሥራ በህገ ወጥ ግብይት ሱፐር ማርኬቱ ላይ ከ60ሺህ ብር በላይ ኪሳራ ማድረሳቸውም ታውቋል።

ፖሊስ ባደረገው ክትትል ሀሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ ደረሠኝ ሲያዘጋጅ የነበረን ሌላ ተጠርጣሪም በቁጥጥር ስር ሊያውል ችሏል።

በሀሰተኛ የሞባይል ባንኪንግ ደረሠኝ አማካኝነት እየተፈፀሙ ያሉ የማታለል ወንጀሎችን ለመከላከል በግብይት ቦታዎች ሸማቾችም ሆኑ ነጋዴዎች የሚላኩላቸውን መልዕክቶች በትኩረት በመከታተልና በመለየት የወንጀሉ ሰለባ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review