በአፍሪካ እግር ኳስ የታሪክ ማህደር ወሳኝ ገፆች መካከል ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ደቡብ አፍሪካ በካርቱም የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የመሰረቱበት የካቲት 8 ቀን 1957 (እ.ኤ.አ) ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በታሪኩ ስኬቶችን እና ውድቀቶችን አሳልፏል። በአንድ በኩል የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ቀዳሚ ውድድር የሆነው የአፍሪካ ዋንጫን ጨምሮ ካፍ በርካታ ውድድሮችን በተሳካ ሁኔታ አዘጋጅቷል። በተጨማሪም ካፍ በአፍሪካ ውስጥ እግር ኳስን ለማዳበር የታቀዱ የተለያዩ ውጥኖችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡
በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 47ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሰሞኑን በዴሞክራቲክ ኮንጎ ኪንሻሳ ተካሂዷል፡፡ ጉባኤው በአፍሪካ እግር ኳስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ቁልፍ ውሳኔዎች የተላለፉበት እና የአህጉሪቱን እግር ኳስ እድገት አቅጣጫ የሚመሩ ስትራቴጂዎች የተቀመጡበት ነበርም ተብሎለታል። አባል ሀገራቱ ለወንዶች፣ ለሴቶች እና ለወጣቶች እግር ኳስ፣ ለዳኝነት፣ ለአመራር እና ለንግድ እድገት የጋራ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን ስለማጽደቃቸውም ከጉባኤው የወጡ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።
ከጉባኤው ከወጡት አስደሳች ነጥቦች መካከል አንዱ ደግሞ ካፍ ከበርካታ ዓመታት ኪሳራ በኋላ ወደ ትርፋማነት መመለሱን የተመለከተው ነው። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ ባወጣው ሪፖርት በ2023/24 የውድድር ዓመት የተጣራ 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አሳውቋል፤ የተከተለው የገንዘብ አስተዳደር እና አዳዲስ ስፖንሰሮች ለዚህ ስኬት እንዳበቁት የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞስፔ ተናግረዋል።
ተቋሙ ባለፉት አራት ዓመታት ከገጠመው የገንዘብ ቀውስ ወጥቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሁን ላይ የካፍ ገቢ ወደ 166 ነጥብ 42 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል። ካፍ ትልልቅ ስም ካላቸው አጋሮች ጋር በመስራት የገንዘብ አቅሙን በማሳደግ ላይ ይገኛል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪነት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ካፍ ገቢውን ለማሳደግ ከተጠቀመባቸው ዋና ዋና መንገዶች ተብለው የተጠቀሱት ንግዱን እና የፋይናንስ አስተዳደሩን ማጠናከር ናቸው። የአፍሪካ እግር ኳስ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት በመጨመሩ፣ ካፍ አዳዲስ ስፖንሰሮችን ማግኘት ችሏል። ለዚሀም የቶታል ኢነርጂስ (Total Energies) በምሳሌነት ተጠቃሽ ነው፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ስፖንሰሮች ቁጥርም በ60 በመቶ ጨምሯል ይላል የአፍሪካ ኒውስ ዘጋባ።
የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሰፔ በስምንት ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ እግር ኳስ የሚውል 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝ የረጅም ጊዜ የግብይትና የቴሌቪዥን ስርጭት ስምምነት ለመጨረስ ካፍ ስለመቃረቡ ገልጸዋል።
በሌላም በኩል ካፍ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማጎልበት ጥብቅ የፋይናንስ ቁጥጥር ስርዓቶችን ተግባራዊ አድርጓል፤ ይህም የገንዘብ ብክነትን ለመቀነስ ረድቷል። ለሁሉም ውሎች የጨረታ ሂደቶችን አስገዳጅ በማድረግ የግዢ ግልጽነትን አጠናክሯል የሚሉት ደግሞ የካፍ ዋና ጸሐፊ ቬሮን ሞሰንጎ ኦምባ ናቸው፡፡ ዋና ፀሐፊው አክለውም እንደገለፁት የገንዘብ አጠቃቀምን በተመለከተ ግልጽነትና ተጠያቂነት በገለልተኛ ኦዲተሮች ቁጥጥር ይደረግበታል ይላሉ።
የገቢው መጨመር ካፍ በእግር ኳስ ልማት ላይ የሚያደርገውን ኢንቨስትመንት በእጅጉ እንዲያሳድግ አስችሎታል። ካፍ በሁሉም ውድድሮች የሽልማት ገንዘብን በእጅጉ ጨምሯል። ለምሳሌ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ሽልማት በ60 በመቶ ጨምሮ 4 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል። የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ (WAFCON) አጠቃላይ የሽልማት መጠን በ45 በመቶ ከፍ ብሎ አሸናፊው 1 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል። ይህ ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ ክለቦችን እና ተጫዋቾችን ያበረታታል፤ የውድድሮቹን ጥራት እና ተወዳጅነት ያጠናክራል።
ካፍ ለአባል ማህበራቱ የሚሰጠውን ዓመታዊ ድጎማ ከ200 ሺህ ዶላር ወደ 400 ሺህ ዶላር ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ የእግር ኳሱ መሰረተ ልማት እንዲሻሻል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም የተቋሙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለአባል ሀገራት ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብም በዋናነት ለወጣቶች ውድድር ማሳደጊያ፣ ለሴቶች እግር ኳስ ልማት እና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፕሮግራሞች እንዲውል ተወስኗል። በአህጉር አቀፍ ውድድሮች (የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ) ለሚሳተፉ ክለቦች እንደዚሁ የገንዘብ ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ከ2025/26 ጀምሮም ለቅድመ ማጣሪያ (Preliminary Rounds) የሚደርሱ ክለቦች እያንዳንዳቸው 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ እንዲያገኙ ተወስኗል።
የካፍ ገቢ እያደገ መምጣቱ በተለይም የአፍሪካ ትምህርት ቤቶች እግር ኳስ ሻምፒዮና በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ፣ የዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን (ስታዲየሞች እና የሥልጠና ማዕከላት) ግንባታን ለመደገፍ እንዲሁም ለዳኞች እና ለአሰልጣኞች የሥልጠና ፕሮግራሞች እንዲስፋፉ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ስለመሆኑ የካፍ ዋና ጸሐፊ ቬሮን ሞሰንጎ ኦምባ አብራርተዋል፡፡
ለቫር መሳሪያዎች ወደ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተመድቧል። እንደዚሁም ይህ የገንዘብ መሻሻል ክለቦችን፣ ተጫዋቾችን እና አባል ማህበራትን በቀጥታ የሚጠቅም በመሆኑ የአፍሪካ እግር ኳስን አጠቃላይ ደረጃ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት ስኬቶች ቢኖሩም ካፍ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እና ግልጽነት እጦትን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች እና ትችቶች አጋጥመውታል። ለአብነትም ድርጅቱ የአፍሪካን እግር ኳስ ተሰጥኦዎች በአግባቡ አውጥቶ መጠቀም ባለመቻሉ በአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ላይ እንቅፋት ሆኗል በሚል ወቀሳ ይቀርብበታል። ከዚህ ባለፈ ካፍ ለአፍሪካ እግር ኳስ ፕሮፌሽናል ማዕቀፍ (ዘመናዊ አሰራር፣ ምልመላና ቅጥር እንደዚሁም የየዕድሜ እርከን ውድድሮች) ለመመስረት አለመቻሉና ይህም በአፍሪካ የእግር ኳስ ደረጃ እንዲቀንስ አድርጓል የሚሉት ጉዳዮች ከትችቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በ47ተኛው የካፍ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ኢንፋንቲኖ ከ2016 ጀምሮ በፊፋ ፎርዋርድ ፕሮግራም አማካኝነት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ በአፍሪካ እግር ኳስ ልማት ላይ መዋሉን ገልጸዋል። የፊፋ ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ የእግር ኳስ መሪዎች “ጠንካራ ድምጽ” እንዲኖራቸው እና ለወደፊት ብሩህ ተስፋ እንዲሰንቁ አንድነታቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላላ ጉባኤው ለአፍሪካ እግር ኳስ የወደፊት ጉዞ ብሩህ ተስፋን ያንጸባረቀ ሲሆን፣ የፋይናንስ መረጋጋት እና የልማት ስራዎች ላይ ያተኮሩ ውሳኔዎች አህጉሪቱ ወደ ከፍተኛ የእግር ኳስ ደረጃ እንድትሸጋገር በር የሚከፍቱ መሆናቸው ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
በሳህሉ ብርሃኑ