AMN – የካቲት 27/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚከሰቱ የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቶችን ከውጭ ዕርዳታ ጥገኝነት በመላቀቅ በሀገር ውስጥ ዓቅም ለመፍታት የሚያስችል የተቀናጀ ስራ እያከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ፅሕፈት ቤት አስታወቀ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንደሙ ሴታ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፤ ከተማዋ ለአደጋዎች ያላትን ተጋላጭነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ፈጣን የሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
በተለይም በአደጋ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የገንዘብ አቅም ለመፍጠር አስተዳደሩ የተለያየ ገቢ እያሰባሰበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የመንግስት ሰራተኞች ከወርሃዊ ደመወዛቸው 1 በመቶ ለድጋፍ ፈንድ እንዲያዋጡ መደረጉን ገልጸው፤ የመንግስት ተቋማትም የበኩላቸውን ድጋፍ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጥላሁን ተክለማርያም በበኩላቸው፤ የዜጎችን ሰብአዊነትና ክብር ለማስጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ በከተማዋ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የድጋፍ ቁሳቁሶችን በአግባቡ ማከማቸት የሚያስችሉ ዘመናዊ ማዕከላትን መገንባቱንም ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አደጋ ለደረሰባቸው ዜጎች በከተማዋ አቅም ብቻ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ማቅረብ መቻሉን ምክትል ኮሚሽነሩ አውስተዋል።
የውጭ ዕርዳታ ጥገኝነትን በዘላቂነት ለመቀነስ እያንዳንዱ ዜጋ፣ ባለሀብቶችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስት ጎን በመቆም የተጀመረውን የ”ራስን በራስ መርዳት” ተነሳሽነት ሊደግፉ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በበረከት ጌታቸው