ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የከተማዋን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአድዋ ድል መታሰቢያ በሚገኘው የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አደራሽ ባካሄደበት ወቅት፤ የምክር ቤቱ አባላት በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በተደረገው ውይይት ሕዝቡ እየተሰራ ባለው የልማት ስራ ደስተኛ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ጥያቄዎቹ የበለጠ እድገትን በመሻት የመጡ እንደሆኑ የምክር ቤት አባላቱ አንስተዋል፡፡ በውይይቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የውሃ አቅርቦት የተመለከተ ይገኝበታል፡፡
ከውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ በጀት ተይዞ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም አሁንም በቂ አቅርቦት የማያገኙ ቦታዎች እንዳሉ ተነስቷል፡፡

ስለሆነም ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለነዋሪዎች ለማቅረብ ከተማ አስተዳደሩ የያዛቸው እቅዶች ምንድን ናቸው? ሲሉ የምክር ቤት አባላት ከነዋሪዎች ጋር በነበረው ውይይት የተነሳውን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በቀረበው ጥያቄ ላይ ምላሽ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ ከተማዋ አሁንም ውሃ በፈረቃ እየቀረበባት እንደሆነ በመግለፅ፤ ይህን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን የነበሩ በዓላት እና ዓለም አቀፍ ኩነቶች፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለሌላ አላማ ማዋል፣ የቁጥጥር ማነስ እና የውሃ አጠቃቀም ብክነት ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ ያነሱት ከንቲባዋ፤ ይህን ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ የአጭር ፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በ2017 ብቻ በቀን 62ሺ ሜትር ኪውብ ተጨማሪ ውሃ ማቅረብ እንደተቻለ የተናገሩት ከንቲባዋ፤ በተያዘውም አመት ተጨማሪ 60ሺ ሜትር ኪውብ በቀን ለማቅረብ ተሰርቷል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በውሃ አቅርቦት በኩል ከለውጡ በኋላ ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሰራ የተናገሩት ከንቲባዋ፤ የጭቋላ እና የገርቢ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በቀን 173 ሺ ሜትር ኪውብ በማቅረብ የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ችግርን የማቃለል አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የከተማዋ የረዥም ጊዜ ችግር የሆነውን የውሃ አቅርቦት በዘለቄታ ለመፍታት ጥናት መጠናቱ እና ወደ ስራ እንዲገባም ፍቃድ ማግኘቱን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ጥናቱን ለማስፈፀም የገንዘብ ማፈላለግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡
የረዥም ጊዜ እቅድ የሆኑት የአለልቱ እና ነጁዶ የሲቪል ውሃ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ አዲስ አበባ በቀን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሜትር ኩብ የውሃ አቅርቦት እንደምታገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ