የአፍሪካ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ሁሉንም ቀጥታ ሃላፊዎችን ያሳውቃል፡፡
ምድብ ሦስት ላይ የምትገኘው ቤኒን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ተቃርባለች፡፡
በቀድሞ የናይጄሪያ አሰልጣኝ ገርኖት ሮኸር የምትመራው ቤኒን ትናንት ምሽት ኬፕ ቨርድ የሰራችውን ታሪክ ለመጋራት ግን ናይጄሪያን ከሜዳዋ ውጪ ማሸነፍ ይጠበቅባታል፡፡
ምድቡ ውጥረት የበዛበት እና ጨዋታዎቹ በጉጉት እንዲጠበቁ የሚያደርግ ነው፡፡ ቤኒን ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ በቀጥታ የማለፍ እድል አላቸው፡፡ ናይጄሪያ ቤኒን ስታስተናግድ ማሸነፍ እና የደቡብ አፍሪካን ነጥብ መጣል ትጠብቃለች፡፡

የካፍ ዝቅተኛ መመዘኛ የሚያሟላ ሜዳ እንኳን የሌላት ቤኒን ድል ከቀናት ማንንም ሳትጠብቅ አዲስ ታሪክ ታፅፋለች፡፡ በተጨዋች ተገቢነት በፊፋ ሦስት ነጥብ ተቀንሶባት አጣብቂኝ ውስጥ የገባችው ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ ሩዋንዳን ማሸነፍ እና የቤኒንን መሸነፍ ትጠብቃለች፡፡
ናይጄሪያ ከ ቤኒን ፣ ደቡብ አፍሪካ ከ ሩዋንዳ በተመሳሳይ ምሽት 1 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ የተወሳሰበ ስሌቱን ይፈታል፡፡ ምድቡን ቤኒን በ17 ነጥብ ስትመራ ፣ ደቡብ አፍሪካ በ15 ናይጄሪያ ደግሞ በ14 ነጥብ ይከተላሉ፡፡
ምድብ ሁለት ላይ 21 ነጥብ የያዘችው ሴኔጋል የዓለም ዋንጫ ትኬቷን ለመቁረጥ ሞሪታኒያን ታስተናግዳለች፡፡ ከሴኔጋል በሁለት ነጥብ አንሳ የተቀመጠችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከሱዳን ጋር ትጫወታለች፡፡ ጨዋታዎቹ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚጀምሩ ይሆናል፡፡
ኮትዲቯር እና ጋቦን የተፋጠጡበት ምድብ ስድስት ዛሬ ይለይለታል፡፡ በ23 ነጥብ የምትመራው ኮትዲቯር ኬንያን ስታስተናግድ ፣ 22 ነጥብ ያላት ጋቦን ብሩንዲን ትገጥማለች፡፡ ሁለቱም ጨዋታዎች ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀምራሉ፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ