የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት በሰላምና ፀጥታ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

You are currently viewing የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት በሰላምና ፀጥታ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
  • Post category:አፍሪካ

AMN ጥቅምት 6/2018

የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ያላቸውን የጋራ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላትን ዛሬ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተቀብለው አነጋግረዋል። ሊቀመንበሩ የምክር ቤቱ አባላትን ሰላም፣ ደህንነት እና ልማትን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ቁልፍ የትኩረት መስኮች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ዩሱፍ የአፍሪካ ህብረት እና የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አጋርነት አፍሪካን በመወከል በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆነው እያገለገሉ ያሉ ሀገራት ማዕቀፍ (A3) አማካኝነት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።

አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ ውክልና ማግኘት እንዳለባት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ሊቀ መንበሩ የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ መር የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን አስመልክቶ ያፀደቀውን የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 2719 በማንሳት የሰላም ማስከበር ስራው ለአፍሪካ ዘላቂ መረጋጋት እጅጉን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የአፍሪካ ህብረትን አመራር ሰጪነት አድንቀዋል። አባላቱ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ሰላም፣ ደህንነት እና ዘላቂ ልማትን ጨምሮ የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የአፍሪካ አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በአዲስ አበባ የጋራ ምክክራቸውን ዛሬ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን ውይይቱ እስከ ነገ ይቆያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review