የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የሚገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተወያየ

You are currently viewing የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የሚገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተወያየ

‎AMN – ጥቅምት 7/2018 ዓ.ም

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (ዲ ኤፍ ሲ) በኢትዮጵያ የሚገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እና የልማት ስራዎችን መደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የአቪዬሽን ዘርፍና ሰፋ ያሉ የኢኮኖሚ ልማት ግቦችን ለመደገፍ ታስቦ የተዘጋጀውን አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ላይ የፋይናንስ ትብብር ማድረግ ላይ አተኩረው መወያየታቸው ተነግሯል።

በቢሾፍቱ ለመገንባት የታቀደው ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት መንገደኞችን የማስተናገድ እና የጭነት አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድግ እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ የሎጂስቲክስ ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል የ ዲ ኤፍ ሲ ሀላፊዎች ተናግረዋል ።

ዲ ኤፍ ሲ ፕሮጀክቱን በገንዘብ ድጋፍ፣ በኢንቨስትመንት ዋስትናዎች እና ከአሜሪካ የግሉ ዘርፍ ኩባንያዎች ጋር በአውሮፕላን ማረፊያ ልማት፣ አቅርቦት፣ ኢንጂነሪንግና ግንባታ ላይ በመተባበር ለመደገፍ ጠንካራ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ ለብሔራዊ ልማትና ለቀጣናዊ ተወዳዳሪነት ወሳኝ በሆነው በኢትዮጵያ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት በተለይም በአቪዬሽን ዘርፍ ዲ ኤፍ ሲ ተሳትፎ ማድረጉን በደስታ እንቀበላለን ብለዋል።

ሁለቱ ወገኖች በአውሮፕላን ማረፊያው እና በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በሚደረግ ድጋፍ ዙሪያ የፋይናንስ አወቃቀር ለማዘጋጀት ውይይቱን ለመቀጠል ተስማምተዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review