የአፍሪካ ቀንድ የፋይናንስ ሚኒስቴሮች የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሩብ ዓመት ስብሰባን በዋሺንግተን ዲሲ አካሂደዋል፡፡
ስብሰባው በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የተካሄደ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ አፈፃፀምን ለመገምገም ፤ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫናዎችን ለመቋቋም ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጠናከር የሚረዱ የፖሊሲ ትግበራዎች ላይ ውይይቱ እንዳተኮረ ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በስብሰባው፤ ከሌሎች ሃገራት ጋር በኤሌክትሪክ የጋራ ተጠቃሚነት ለማስፈን ምቹ ሁኔታን ስለፈጠረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንስተዋል ።
አክለውም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የንግድ ስምምነትም በቀጣናው ሃገራት መካከል የንግድ እንቅስቃሴን ከማሳደግ ባሻገር አህጉራዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን እውን እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ያላትን ቁርጠኝነት የገለፁት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የዓለም ባንክ እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እያደረጉት ላለው ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሊያት ካሳሁን