የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ባንክ እና የአይ ኤም ኤፍ ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን በቪ20 የሚኒስትሮች ውይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በዚሁ ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አሕመድ ሽዴ ለአየር ንብረት ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት አስቸኳይ እና አፋጣኝ ትኩረት እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡
በነዚሁ ሀገራት ጎርፍ እና ድርቅን ጨምሮ ሌሎች አደጋዎች የህዝብ ፋይናንስ ጫና ውስጥ እንዲወድቅ ማድረጉን አስገንዝበዋል፡፡
የአየር ንብረት ተጋላጭነት እየጨመረ ከመጣው ዕዳን የማስጠበቅ ግዴታዎች ጋር ተዳምሮ ሀገራቱ ያገኙትን የልማት እና የአቅም ግንባታ ጥረቶችን እንደሚሸረሽርም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዝቅተኛ የካርቦን እና የማይበገር የአየር ንበረት ለውጥ ግንባታን በመከተል በአፍሪካ ከቀዳዊዎቹ መካከል እንደምትገኝ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እና በመላው ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ ደኖችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እንዲኖራቸው ለማስቻል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በስፋት መከናወኑንም አንስተዋል፡፡
በተለይም መንግስት የወሰዳቸው የአረንጓዴ ሽግግር ፖሊሲዎች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል የተገኘ የኃይል ውህድ 95 በመቶ ላይ እንዲገኝ አስችሏል ብለዋል፡፡
መሰል ጥረቶች ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደሚሹ ሚኒስትሩ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡ በተለይም ኮንሴሽናል ፋይናንስ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን እና የአየር ንብረት ለውጥ እርዳታዎችን በማስፋት ሀገራት የእዳ ሸክማቸው ሳያሳስባቸው መቋቋም እንዲችሉ ድጋፍ እዲደረግም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ኢትዮጵያ የበለጠ ፍትሀዊ፣ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባት ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡
በማሬ ቃጦ