የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት፣ የስራ ዕድል ፈጠራና ከተረጅነት የመላቀቅ ግቦችን ለማሳካት የባለድርሻ ተቋማት ቅንጅት ሊጠናከር እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ ።
የብልጽግና ፓርቲ 2018 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል፡፡
በመድረኩ በመንግሥት ስራዎች አፈጻጸም ላይ ውይይት እየተካሄደ ሲሆን የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም ከተረጅነት የመላቀቅ ግቦች በአጀንዳነት ቀርበዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እንዳሉት፤ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋትና ስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት የሚሹ አንገብጋቢ አጀንዳዎች ናቸው፡፡
ከተረጂነት መላቀቅ የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መንገድ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ላይ በተቀናጀ አግባብ መስራት እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሦስቱንም ሀገራዊ ግቦች በተሟላ መልኩ ለማሳካት የባለድርሻ ተቋማት ቅንጅት ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በአፈጻጸም ደረጃ እንደ ሀገር ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው ከአካባቢ አካባቢ ያለውን የአፈጻጸም ልዩነት ለማጥበብ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በዘርፉ ውጤታማነትን ለማሳደግ በጋራ ማቀድ እና አፈጻጸሞችን በጋራ በጥልቀት እየገመገሙ መሄድ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡