AMN ጥቅምት 14 /2018 ዓ.ም
በሚቀጥሉት ወራት ለመመረቅ ወረፋ የሚጠብቁ ግድቦች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አድርገዋል።
በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ኢትዮጰያ ውስጥ የመፍጠር እና መፍጠን አስፈላጊነት በግልጽ መታየት መጀመሩን ገልፀዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ኘሮጀክቶች መኖራቸውን ገልፀው፣ እንዲሰሩ መከታተልም ከተጠናቀቁ በኃላ ማስመረቅም ስራ እየሆነ መምጣቱን አመላክተዋል።
በርካታ ኘሮጀክቶች የማስመረቅ ጥያቄ ቢቀርብም በኘሮግራም መጣበብ ምክንያት እንደሚቸገሩ ነው የገለፁት።
ለአብነት የግድብ ፕሮጀክቶችን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ሶማሌ ክልል የሚገኘው ግድብ፣የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ወልመል፣ መመረቃቸውን እና በሚቀጥሉት ወራት ደግሞ ለመመረቅ ወረፋ የሚጠብቁ ግድቦች መኖራቸው አስረድተዋል።
እነዚህ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የሚባሉ ግድቦች መሆናቸውን፣ ለመስኖ እና የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያመነጩ ያለቁ እና ምርቃት የሚጠብቁ ኘሮጀክቶች እንደሆኑ ገልፀዋል ።
ወደ እንደዚህ አይነቱ አውድ ያስገባን መፍጠር እና መፍጠን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንፍጠን እንትጋ ከልፋታችን ውጪ የሚለወጥ ሀገር አይኖርም የሚለው እሳቤ በእጅጉ ማገዙን ነው የገለፁት።
በሔለን ተስፋዬ