የሁለገቡ ከያኒ አበርክቶ ሲታወስ

You are currently viewing የሁለገቡ ከያኒ አበርክቶ ሲታወስ

ተወርዋሪ ኮከብ…

በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ                የጠፋ፣

ተወርዋሪ ኮከብ…

በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ፡፡

ይሄ ግጥም የታላቁ ገጣሚ የዮሃንስ አድማሱ ነው፡፡ ዮሃንስ ይሄን “ተወርዋሪ ኮከብ” የተሠኘው ድንቅ ግጥም የጻፈው ከእሱ በፊት ለነበረው ለታላቁ ባለቅኔና ፀሃፌ-ተውኔት ዮፍታሄ ንጉሴ ነበር፡፡ ግጥሙ ለሌላኛው ታላቅ አርቲስት ስዩም ወልዴ ራምሴም የሚስማማ ነው፡፡

ስዩም ወልዴ በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ሰማይ ስር ከታዩ ተወርዋሪ ኮከቦች መካከል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ መድረክ ላይ እንደ ኮከብ አንጸባርቋል፡፡ ኪነ ጥበባዊ ተሰጥኦን ከቀለም ትምህርት ጋር በማሰናኘት በኢትዮጵያ ኪነ ጥበባዊ ጉዞ ላይ የማይዘነጉ ጥበባዊ አሻራዎቹን አስቀምጧል፡፡ በሰዓሊነት፣ በመምህርነት፣ በጋዜጠኝነት፣ በሃያሲነትና በሌሎችም ሙያዎች ኹነኛ ከያኒነቱን በሚገባ አስመስክሯል፡፡ በዚህ የጥበብ ዓምድም ታላቁ ሰዓሊ፣ መምህር፣ ጋዜጠኛ፣ ሃያሲ፣ ፀሃፌ-ተውኔት፣ የሥነ ጥበባት ታሪክ ተመራማሪ እና የልብስ ዲዛይነር ሥዩም ወልዴ ራምሴን በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡

ሥዩም ወልዴ ራምሴን በኪነ ጥበብ መድረክ

ሥዩም ወልዴን እንደ አንድ ግለሰብና እንደ ሁለገብ ከያኒ በሚገባ ለማወቅ በወርሃ ጥር፣ 1985 ዓ.ም ‘ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ’ የተሰኘው መጽሐፉን ማንበብ የግድ ይላል፡፡ ይሄ መጽሐፍ የአርቲስት ስዩም ወልዴ ግለ ታሪክ (ኦቶባዮግራፊ) ነው፡፡ አርቲስቱ ግለ ታሪኩን ለትውልድ ትቶ ያለፈው፣ የአንድን ከያኒ የፈጠራ ሥራና ህይወት ከሀገር ታሪክ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚተሳሰር በመገንዘቡ ይመስላል፡፡ ይሄን የአርቲስቱ ግለ ታሪክ መጽሐፍ ስለ ሥዩም ወልዴ ከያኒነት፣ ሁለገብ ሙያተኛነትና ህይወቱ ምን ይመስል እንደነበር ለመረዳት እጅግ ወሳኝ ሰነድ ነው፡፡ ይሄን ጽሑፍ በምናዘጋጅበትም ጊዜ ይሄንን መጽሐፍ በዋና ምንጭነት ተጠቅመነዋል፡፡

ሥዩም ወልዴ ሰዓሊ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ሰዓሊያን መካከልም አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ እንደ ሁለተኛ ትውልድ ከሚታዩት የተከበሩት የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ገጣሚና ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ እና ከሰዓሊ እስክንድር ቦጎስያን ጋር የአንድ ዘመን ተጋሪ ከያኒ ነው፡፡

ስዕል የመሳል ትልቅ መሻትና ተሰጥኦ የነበረው ብላቴናው ሥዩም፤ ይሄንን መሻቱን በዘመናዊ ዕውቀት ለማስደገፍ ከሀገር ውስጥ ጨምሮ እስከ ሩሲያ (የዚያን ጊዜ ሶቪየት ሕብረት ትባል ነበር) ሞስኮ ድረስ ሄዶ ተምሯል፡፡ ከሞስኮ ከተመለሰም በኋላ ሥነ ጥበብን አስተምሯል፡፡

አርቲስት ስዩም የትምህርት ዕድል አግኝቶ ሞስኮ ከመሄዱ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የራሱን የሥዕል ዓውደ ርዕይ ማሳየት የቻለ አርቲስትም ነው፡፡ ስዩም በሀገር ውስጥ በግልና ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በመሆን ተደጋጋሚ የሥዕል ዓውደ ርዕዮችን ለጥበብ አፍቃሪያን አቅርቧል። ካቀረባቸው ኤግዚቢሽኖች መካከል በሐምሌ 1955 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል በግሉ ያቀረበው የሥዕል አውደ ርዕይ ይገኝበታል፡፡ ይሄ አውደ ርዕይ ለሥዩም የመጀመሪያው አውደ ርዕዩ ነው፡፡ እሱም የመጀመሪያው በመሆኑ በከያኒነት ሕይወቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አውደ ርዕይ ነው፡፡ አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱት በጊዜው የትምህርት ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር መንገሻ ገብረሕይወት ነበሩ፡፡ ስለዚህ ኤግዚቢሽን አርቲስት ሥዩም ‘ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ’ በተሰኘው መጽሐፉ በገጽ 89 እንዲህ ሲል አስፍሯል፤ “በሐምሌ ወር አጋማሽ ኤግዚቢሽኑ ተከፈተ፡፡ በዱብ ዕዳ ሠዓሊ ተባልኩና ስሜ በየጋዜጣው፣ በየሬድዮውና በቴሌቪዥን ተደጋግሞ ተጠራ፡፡ ካዘጋጀኋቸውም አርባ ሥምንት ሥዕሎች መካከል ወደ ሃያ ስድስቱ ተሸጡ፡፡ ይሄ ለእኔ ትልቅ ስኬት ነበር፡፡”

ከዚህ አንጻር ስዩም ገና ከመነሻው ነው በሥዕል ጥበብ ዕውቅናን ያተረፈው። ከዚህ የሥዕል ዓውደ ርዕይ በኋላ በግሉ ሌሎች የሥዕል አውደ ርዕዮችን አሳይቷል። በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በመሆን በ1969 ዓ.ም እና በ1970 ዓ.ም አሳይቷል። ሥዩም ወልዴ በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን በውጭ ሀገራትም የሥዕል ዓውደ ርዕዮችን ማሳየት የቻለ ሰዓሊ ነው፡፡ ለአብነትም በሩሲያ ሞስኮ ተማሪ እያለ በ‘ሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ’  በግሉ በ1966 ዓ.ም እና በ‘ሞስኮ ፍሬንድሽፕ ሃውስ’  በ1967 ዓ.ም የሥዕል ሥራዎቹን አሳይቷል፡፡

የዚህ አይነቱ የላቀ ተሰጥኦ የነበረው አርቲስት ሥዩም የሙሉ ጊዜ ሰዓሊ ግን አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ ከሌሎች ሙያዎች ጋር በጎን የሚያስቀጥለው ሙያ ነበር፡፡ የሚያስገርመው ነገር አርቲስት ሥዩም ምንም እንኳን ከፍተኛ የሥነ ጥበብ ተሰጥዖና ዝንባሌ ቢኖረውም ከሰዓሊነት በጊዜ ነው የተገለለው፡፡ ከዚያ በኋላ ሥነ ጥበባዊ ሥራዎችን ወደ መሄስ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሥነ ጥበብን ወደ ማስተማር ፊቱን አዙሯል፡፡

ሥዩም ወልዴ ሃያሲም ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ፈርቀዳጅ ሃያሲያን መካከል እንደ አንዱ የሚታይ ሃያሲም ጭምር፡፡ ሥነ ጥበብን በዕውቀት በመሄስና ዘመናዊ የሃያሲነት ስልት ለኢትዮጵያ ካስተዋወቁ ታላላቅ ሰዎች መካከልም ይመደባል፡፡ ሥነ ጥበብን በዕውቀት በመሄስ ከገጣሚ ሰሎሞን ዴሬሳ ቀጥሎ የሚጠቀሰው ይኸው ሁለገቡ አርቲስት ስዩም ወልዴ ነው፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛ ዲበኩሉ ጌታነህ ስለ አርቲስት ሥዩም ወልዴ ለዝግጅት ክፍላችን ባጋራን መረጃ፣ ስዩም ወልዴ ራምሴ ሁለገብ አርቲስት መሆኑን አጫውቶናል፡፡ በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ላይ ብቃቱን በሚገባ ማስመስከሩን በመግለጽ በተለይም ዘመናዊ የሂስ መንገድ አስቀድመው ከተለሙልን ቀደምት ከያኒያን መካከል አንዱ እንደሆነም ተናግሯል፡፡

ብዙዎች ስዩምን የሚያስታውሱት በሰዓሊነቱ ነው የሚለው ደራሲና ጋዜጠኛ ዲበኩሉ፣ ከዚህ ባሻገርም ስዩምን “ሥነ ጥበብን በማስተማርና ሥነ ጥበብን ለማሳደግ የሚያስችሉ የጥበብ ማህበራትን በመመስረት ሥነ ጥበብን ተቋማዊ ገፅታ እንዲይዝ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከሁሉም በላይ ሥዩምን ስናስታውስ መዘንጋት የሌለበት አንድ ጉዳይ የሥዩም ወልዴ የሃያሲነት ብቃትን ነው፡፡ ሥዩም ወልዴ በየካቲት መጽሔትና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ያደረጋቸው ሥነ ጥበባዊ ሂሶች ዛሬም ድረስ በተመራማሪዎች እንደማጣቀሻ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ሥነ ጥበብን መሄስ ትልቅ ንባብ፣ አስተውሎትና የመጻፍ ችሎታ እንደሚጠይቅ ለመረዳት የሥዩም ሂሳዊ መጣጥፎችን ማንበብ በቂ ነው። ከዚህ አንጻር ሥዩም በሃያሲነቱ፣ በሰዓሊነቱና በመምህርነቱ አንቱታ የሚገባው ታላቅ አርቲስት ነው” በማለት አጫውቶናል፡፡

ስዩም ወልዴ ጋዜጠኛም ነው፡፡ ወደ ጋዜጠኝነት የገባው ባጋጣሚ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን በጊዜው በሙያው እጅግ ከታወቁ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ሥዩም በ1958 ዓ.ም ነበር ‘ብሥራተ ወንጌል’ ይባል በነበረው ሬዲዮ ጣቢያ በባህልና በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች አዘጋጅነት የጋዜጠኝነት ሙያ መስራት የጀመረው፡፡

በሙያው በጊዜው ታላላቅ የመንግስት ባለሥልጣናትን ቃለ መጠይቅ ከማድረግ አንስቶ፤ የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልሱ በርካታ የሬድዮ ፕሮግራሞችን ሰርቷል። በግለታሪክ መጽሐፉ በተደጋጋሚ እንዳሰፈረው በጊዜው የጋዜጠኝነት ሙያ ታላቅ አክብሮት እና ዕውቅና አስገኝቶለት እንደነበር ጽፏል፡፡

ከሙያው ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ ይገጥመው የነበረ ተደጋጋሚ ክስተት እዚህጋ እንጥቀሰው፡፡ በሬድዮ ድምጹንና የፕሮግራሙን ብስለት ያደመጡ ባለስልጣናት እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች በአካል ለቃለ መጠይቅ ቀጥረውት ሲሄድ ተደጋጋሚ ገጠመኝ ገጥሞታል፡፡ በሬድዮ ድምጹንና ፕሮግራሙን የሚሰሙ ሰዎች ወጣቱን ስዩም በእድሜ እና በትምህርት የገፉ ትልቅ ሰው አድርገው ነበር የሚያስቡት፡፡ ቃለ መጠይቅ ሊያደርግ ሄዶ በተደጋጋሚ “ሥዩም ወልዴ እርሶ ሊሆኑ አይችሉም” ተብሎ መታወቂያ ተጠይቆ ያውቃል፡፡ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው ሥዩም ወልዴ በጊዜው ዝነኛና ተወዳጅ ጋዜጠኛ እንደነበረ ነው፡፡ ሩሲያ ሞስኮ የትምህርት ዕድል አግኝቶ እስከሄደበት ጊዜ ድረስ በጋዜጠኝነት ሙያ አንቱታን አትርፎለታል፡፡ ከዚህ አንጻር ሥዩም ወልዴ ኹነኛ ጋዜጠኛም ነው፡፡

ሥዩም ወልዴ ሞስኮ ለሰባት ዓመታት ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ሀገሩ ከተመለሰም በኋላ ስነ ጥበብን አስተምሯል፡፡ ከአርቲስት ሥዩም የቀድሞ ተማሪዎች መካከል በአሁኑ ሰዓት በሙያው አንቱታን ያተረፈው ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን (ተባባሪ ፕ/ር) አንዱ ነው፡፡ በአንድ ቃለ መጠይቁ ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን ስለ ቀድሞ መምህሩ እንዲህ ብሏል፤ “ስዩም ወልዴ ብቁ መምህር ነበር። ወደ መማሪያ ክፍል ሲገባ ተዘጋጅቶ በፍጹም ራስ መተማመን ያስተምር ነበር። መምህር ስዩም ሲያስተምረን ብዙ ጽሑፍ ያፅፈን ነበር። የፈላስፋዎችን ታሪክ እጃችንን እስኪያመን ድረስ ያፅፈን ነበር። አሁን ላይ ሳስበው ሰው የፃፈውን አይረሳምና እንድናስታውስ አድርጎናል። ስዩም በስራ ላይ ደራርቦ እየሰጠን ያጠነክረን ነበር” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

ከዚህ አንጻር ስዩም ወልዴ ከቀዳሚዎቹ ሰዓሊያን፣ ሃያሲያን፣ የሥነ ጥበብ ተመራማሪዎችና መምህራን መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡ አርቲስት ስዩም ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሠዓሊያንና በኢትዮጵያ ደራሲያን አንድነት ማህበራት በዋና ፀሐፊነትም ለዓመታት አገልግሏል።

ሥዩም ወልዴ ራምሴ ማነው?

ሥዩም ወልዴ የፒያሳ ልጅ ነው። ለዚያውም አዲስ አበባ መሃል አራዳ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ጎን ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ ሥዩም በ1935 ዓ.ም ነበር ይህን ዓለም የተቀላቀለው፡፡ ሥዩም መሃል አዲስ አበባ ተወልዶ ቢያድግም በዚያ ጊዜ ባህል መሰረት ከቤቱ አቅራቢያ ከሚገኘው የቄስ ትምህርት ቤት ሄዶ ተምሯል። የየኔታ አለንጋንም በደንብ ቀምሷል፡፡ እንዲያውም ስዩም በግለ ታሪኩ ይህንን አለንጋ እንደ መልካም ትዝታ ሳይሆን፤ እንደ መጥፎ ትውስታ ነው የጻፈው። በኋለኛው የዕድሜ ዕርከን ላይ የየኔታ አለንጋ ተጽዕኖ አድርጎበት ትምህርት ቤት አልሄድም ብሎ እስከማመጽና ትምህርት እስከመጥላት እንደደረሰም ጽፏል፡፡ የራሱን የልጅነት ልምድን መነሻ በማድረግ ልጆችን በዕውቀት ለመቅረጽ ከአለንጋ ይልቅ ጥበብ የታከለበት ብልሃት እንደሚያስፈልግም በግለ ታሪኩ ውስጥ አስፍሯል፡፡

ሌላው ስለ ስዩም ወልዴ የሚያስደንቀው ነገር አስተዳደጉ ነው። አስተዳደጉ ከስራ ጋር ጥብቅ ትስስር አለው፡፡ ስዩም ገና ከለጋ ልጅነቱ ጀምሮ ነው ከስራ ጋር የተዋወቀው፡፡ ከቤቱ ጎን ከሚገኘው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ውስጥ መጋረጃን የመክፈት የመዝጋት ሥራ እየተከፈለው ሰርቷል፡፡ መርካቶ ውስጥ እቃ ዘርግቶ ሸጧል፡፡ ከልብስ ሰፊነት አንስቶ የሰርግና የሀገር ባህል ልብሶችን ዲዛይን የማድረግ ስራ ሰርቷል።

አርቲስት ሥዩም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኃላ በሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ታሪክ፣ የጥበብ ንድፈ ሃሳብና የሃያሲነት ትምህርቶችን በመማር በማስተርስ ዲግሪ ተመርቋል፡፡

ስዩም የአርበኛ ልጅ ነው፡፡ አባቱ አቶ ወልዴ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም በቆየው የጣሊያን ወረራ ጊዜ ትግራይ ምድር ድረስ ተጉዘው ሀገራቸውን ከጠላት ወረራ ለመታደግ ዘምተዋል፡፡ በማይጨው ጦርነትም ተሳትፈዋል፡፡

 አርቲስት ሥዩም ከላይ ከተጠቀሱት የጥበብ ዘርፎችና ሙያዎች በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ “የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት” ይባል በነበረው ተቋም ውስጥ፣ በባሕል ጉዳዮች ዋና ኤክስፐርትነት ሆኖ ሀገሩን አገልግለዋል። በአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት የሥነ ጥበብ ታሪክን አስተምሯል። ተወርዋሪው ኮከብ ሥዩም ወልዴ ራምሴ ከውልደቱ አንስቶ ሕይወቱ እስካለፈበት 1990 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መስኮች ሀገሩን አገልግሏል፡፡ ለትውልድ የሚጠቅም ሥራ በመስራቱ፤ ይኸው እኛም ከህልፈተ ሕይወቱ ሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ታላቁ አርቲስት ሥዩም ወልዴ ራምሴን በዚህ መልኩ አስታወስነው፡፡  

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review