የአርሰናል የቀድሞ አማካይ አሌክስ ኦክሲላዴ ቻምበርሊን ከመድፈኞቹ ወጣት ቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰራ ታይቷል፡፡ የሳውዛምፕተን አካዳሚ ውጤት ቻምበርሊን እንዴት ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመለሰ? ብዙዎችን ግራ ያጋባ ክስተት ሆኗል፡፡
የ32 ዓመቱ ቻምበርሊን ከቱርኩ ክለብ ቤሽኪታሽ ጋር የነበረውን ውል አቋርጦ ማረፊያ ሲያፈላልግ ነበር፡፡ አርሰናል ደግሞ ጊዜያዊ ማቆያው ሆኖ ከወጣት ቡድኑ ጋር ልምምድ እንዲሰራ ፈቅዶለታል፡፡
ቻምበርሊን እንዴትና? ለምን? አርሰናልን እንደተቀላቀለ የተጠየቀው ሚካኤል አርቴታ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ሚካኤል አርቴታና ኦክሲላዴ ቻምበርሊን በ2011 አንድ ላይ ነበር አርሰናልን የተቀላቀሉት፡፡ የዛሬው አሰልጣኝ አርቴታና ቻምበርሊን ለበርካታ ዓመታት ለአርሰናል አብረው ተጫውተዋል፡፡ በደምብ ይተዋወቃሉ፡፡
“ምርጥ ባህሪ ነው ያለው፣ ቻምበርሊንን ወደ ቀድሞ ብቃቱ ለመመለስ ከአርሰናል በላይ ኃላፊነት ያለበት የለም፣ ቻምበርሊን ለታዳጊ ተጨዋቾች አርአያ መሆን የሚችል ተጨዋች በመሆኑ ከወጣት ቡድናችን ጋር እንዲሰለጥን ፍቃድ ሰጥተንዋል” ብሏል ስፔናዊ አሰልጣኝ አርቴታ፡፡
አሌክስ ኦክሲላዴ ቻምበርሊን ለሰሜን ለንደኑ ክለብ 198 ጨዋታዎችን አድረጎ 20 ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ በፈረንጆቹ 2017 በ35 ሚሊዮን ፓወንድ ሊቨርፑልን መቀላቀሉ የሚታወስ ነው፡፡
በታምራት አበራ