አዲስ አበባ ሀገራዊ ስኬቶችን መቁጠር ችላለች

You are currently viewing አዲስ አበባ ሀገራዊ ስኬቶችን መቁጠር ችላለች

AMN – ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የልማት ስራዎች በሃገር ደረጃ ትላልቅ ስኬቶችን መቁጠር ለመቻላችን ማሳያ ነዉ ሲሉ የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ።

የከተማዋን የልማት ስራዎችን በተደጋጋሚ ጊዜ የመጎብኘት እድል ማግኘታቸውን የገለጹት አቶ አወል አርባ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች እንደ ሀገር አንገታችንን ቀና እንድናደርግ የሚያግዙ ናቸዉ ሲሉ ገልፀዋል ፡፡

የልማት ስራዎቹ ሰው ተኮር መሆናቸው እና ሁሉንም ዜጎች ማዕከል ያደረጉ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም መዲናዋን የቱሪዝም መዳረሻ አድርጓታል ሲሉ ተናግረዋል ።

በመዲናዋ የተገነቡ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗም ባሻገር በአፍሪካ ተመራጭ ከተማና የቱሪዝም ማዕከል መሆኗን የሚያረጋግጥ ነዉ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን ያሉትን አባባል በርግጠኝነት ትላንት በኦሮሚያ ክልል ዛሬ ደግሞ በአዲሰ አበባ ከተማ ያየነው የልማት ስራ አመላካች ነው ሲሉ ተናግረዋል ።

በከተማዋ ያዩት የገጠር እና የከተማ የምርት ትስስር እንዳስደነቃቸው ም ገልፀዋል ፡፡

ባለፉት ጊዜያት ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ ያልነበረች፣ በሰዎች በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩባት፣ ሕጻናት የሚጫወቱበት ስፍራ ያልነበራት እና ለመኪኖች እና ለዜጎች እንቅስቃሴ ያልተመቸች እንደነበር ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት በየቦታው መዝናኛዎች መኖራቸውን እና በተለይ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለዚህ ምቹ ሆኖ መሰራቱ በጣም የሚያስደስት መሆኑን ነው የተናገሩት ።

በመሆኑም በጉብኝቱ ያገኙትን ልምድ እና ተሞክሮ እሴት ጨምረው በክልላቸው እየሰሩበት መሆኑን አመላክተዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review