የትርፍ አንጀት በትልቁ አንጀት ጫፍ ላይ የሚገኝ የሰውነት ክፍል ሲሆን፤ ከ2 እስከ 8 ሴንቲ ሜትር ርዝመት አለው፡፡
ትርፍ አንጀት ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ባክቴሪያዎችን እንደሚያስጠልል እና የበሸታ መከላከል ሥርዓትን እንደሚደግፍ በዘርፉ የወጡ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ትርፍ አንጀት በሁሉም ሰው ላይ የሚገኝ ትርፍ ስጋ ሲሆን፤ የትርፍ አንጀት ጫፍ ሲዘጋ የሚፈጠረው ብግነት ወይም ቁስለት በቶሎ ካልታከመ በመፈንዳትና ወደ ሆድ እቃ በመሰራጨት እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡

የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሃያት ጋቢሣ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በትልቁ አንጀት ጫፍ ላይ የሚገኘው ትርፍ አንጀት መንስኤው የሆድ ድርቀት፣ ባዕድ ምግብ ወደ ሆድ ሲገባ፣ የሆድ ትላትሎች እና በሆድ አካባቢ የሚገኙ ዕጢዎች ሲቆጡ የትርፍ አንጀት ጫፍን በሚዘጉበት ወቅት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እነኚህ መልክቶችን ተከትሎ የትርፍ አንጀት ጫፍ በመቁሰልና ኢንፌክሽን በመፍጠር ወደ ሆድ ዕቃ በመሰራጨት ህመም እንደሚፈጥርም ገልፀዋል፡፡
ድንገተኛ የሆድ ቁርጠት፣ በቀኝ ጐን በኩል አጣዳፊ ውጋት፣ ማስመለስ፣ ማቅለሽለሽ፣ የምግብ ፍላጐት ማጣት፣ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የሆድ ድርቀት እና አንዳንዴም ተቅማጥ የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡

በአጣዳፊነቱ የሚታወቀው የትርፍ አንጀት በሽታ የሚታከመው በቀዶ ጥገና ብቻ ሲሆን በቶሎ ካልታከመ ለሞት የሚዳርግ በሽታ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከቀዶ ጥገና በኋላ በዛ ያለ ፈሳሽ መውሰድ፣ ለመፈጨት ቀላል የሆኑ እና ለስለስ ያሉ ምግቦችን መመገብ፣ በቂ እረፍት ማድረግና ቀለል ያለ እንቅስቃሴ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሃያት ጋቢሣ ገልፀዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው