የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‘ሲ.ቢ.ኢ በእጄ’ የተሰኘ የዲጂታል ብድርና ቁጠባ አገልግሎትን አስጀመረ።
አገልግሎቱ የቀረበው ወርሀዊ ደመውዝ በሲቢኢ ብር ለሚከፈላቸው ደንበኞች ሲሆን፣ ያለምንም ማስያዣ ከ500 እስከ 150ሺህ ብር ድረስ መበደር የሚችሉበት ስለመሆኑም ተገልጿል።
በመርሀግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዘዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፤ የኢትየጵያ ንግድ ባንክ በመደበኛው የባንክ አገልግሎት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም ባንኩ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት በማስተዋወቅ ረገድም ቀዳሚ ሆኗል ብለዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መንገድ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋፋት፣ የሀገሪቱን የዲጂታል ክፍያ ስርአት እድገት በከፍተኛ ፍጥነት ወደፊት እንዲራመድ አስችሏልም ብለዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት እንደ ሀገር ከ17.7 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውርና ክፍያ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች እንደተፈጸመ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ13 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ግብይት የተከናወነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል አማራጮች በኩል ነው ያሉ ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላዩ ግብይት 73 ከመቶው ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የዲጅታል አገልግሎቱ ለ9 ወራት በሙከራ ላይ እንደቆየና በራስ አቅም የተሰራ ስለመሆኑም ባንኩ አስታውቋል።
በቶማስ አሊጋዝ