በህብረት ስራ ማህበራት ላይ የማሻሻያ ስራ በመሰራቱ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተጫነ አዱኛ ገልጸዋል ።
ህብረት ስራ ማህበራቱ ያለባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኮሚሽን የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የሪፎርም ስራው ማህበራቱን በብቁ አመራር የማደራጀት ፣ አገልግሎት አሰጣጣቸው ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተጫነ አዱኛ ለኤ ኤም ኤን አስረድተዋል።

የሪፎርሙ ስራው በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ፣ ለአሰራር ማነቆ የሆኑ የህግ ማእቀፎችን በማሻሻል እና የህግ ማእቀፍ ለሌላቸው የህግ ማእቀፎች የማዘጋጀት ስራዎች እንዲከናወኑ ዕድል መፍጠሩን ያመላከቱን ምክትል ኮምሽነሩ ደንብ ቁጥር 170 እና 171/2016 ዓ.ም ሆኖ ፀድቆ በስራ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
እነዚህ ደንቦች ከአሰራር ማዕቀፎች እንፃር የነበሩ ክፍተቶችን የሚሞሉ እንደሆኑ አስረድተው ፣ሪፎርሙ በተለይም የአሰራር ስርዓትን በቴክኖሎጂ ከማዘመን አኳያ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል ።
አሰራሮችን ለማዘመንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር መዘርጋቱንንና በዚህም ተጨባጭ ለጦውች መመዝገባቸውን ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የተናገሩት ።
የሸማች ህብረት ስራ ማህበራቱ ሰፊ ሀብት ያላቸው ሲሆን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከ2 ሺህ 700 የሚበልጡ የህዝብ መዝናኛዎችን እንዲያስተዳድሩ ከተማ በከተማ አሰተዳደሩ እንደተሰጣቸውም አቶ ተጫነ አዱኛ ተናግረዋል ።
ማህበራቱ የዋጋ ንረትን ከማረጋጋት አኳያ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ መሰረታዊ ፍጆታንና የግብርና ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ጀምሮ የተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍተኛ በሚሆንባቸው የበዓላት ወቅት ላይ በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል ።
የማህበራቱን ዓቅም ለማሳደግ የከተማ አስተዳደሩ የድጎማ በጀት በመመደብ የግብርና እና የኢንደስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለህብረተሰቡ እንዲደርስ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በሔለን ተስፋዬ