ኢትዮጵያ ከተቸሯት ፀጋዎች እና ጎልታ እንድትታይ ከሚያደርጓት ሀብቶቿ አንዱ የብዝሃ ማንነት እና የብዝሃ ቋንቋዎቿ ባለቤት መሆኗ ነው።
የኢፌድሪ ህገ-መንግስትን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን፣ ባለፉት 19 ዓመታት አንድነትን በማጠናከር እና የእርስ በእርስ ትውውቅን ከፍ በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ዘንድሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ “ዲሞክራሲያዊ መግባባት፣ ለህብረብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓሉ፣ በአዲስ አበባም ህገ-መንግስታዊ አስተምህሮ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ከወረዳ እስከ ከተማ እንደሚከበር የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሪት ፋይዛ መሃመድ ተናግረዋል።
የዲሞክራሲ ፅንስ ሃሳብ፣ የህዝብ ትስስርን እና አንድነትን ለማምጣት፣ በፌዴራሊዝም ዙሪያ ህገ-መንግስቱ ላይ ያሉትን መብቶች ለህዝቡ ለማስረጽ፣ ምክር ቤቱ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሪት ፋይዛ መሀመድ ገልፀዋል፡፡

ማህበረሰቡ የብሔር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ምንነትና አስፈላጊነት ግንዛቤ ኖሮት እንዲያከብር ግንዛቤ እንደሚፈጠርም ተናግረዋል።
በፈጣን የልማት ጎዳና ላይ በምትገኘው አዲስ አበባ ከተማ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር የጎብኝዎችን ቁጥር ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑንም ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ተክሌ ዲዱ፣ በፌዴራሊዝም እና ህገ-መንግስቱ ላይ የግንዛቤ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ አንሰትው፣ ይህንን የግንዛቤ ክፍተት ለመቅረፍ የፌዴራል ስርዓቱ አስተምህሮ ላይ ከ1.5 ሚሊዮን ያላነሰ ህዝብ በአስተምህሮ የሚሳተፍበት፣ ተማሪዎች ጥያቄ እና መልስ ውድድር የሚያደረጉበት፣ ሰፊ የንቅናቄ ስራ በከተማ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔሮች ብሔረሰቦች በዓል መከበር፣ የማንነት መገለጫ ለሆኑት ለባህል እና ኪነ-ጥበቡ ዕድገትና እንዲሁም ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አይነተኛ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል፡፡
ዘንድሮ የሚከበረውን 20ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦች በዓል አስመልክቶ በከተማ ደረጃ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ሰልጣኞች ዲሞክራሲ እና ህብረብሔራዊነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ስልጠና መሰጠቱም ተገልጿል።
በፍሬህይወት ብርሃኑ