የመርሳት ህመም እንዴት ይከሰታል? የህመሙ ምልክቶች እና ህክምናውስ?

You are currently viewing የመርሳት ህመም እንዴት ይከሰታል? የህመሙ ምልክቶች እና ህክምናውስ?
  • Post category:ጤና

AMN- ህዳር 04/2018 ዓ.ም

‎በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት ዕድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ተጓዳኝ ህመሞች ይከሰትባቸዋል።

‎በተለይ በዚህ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች የተለመዱ የመገጣጠሚያ፣ የጡንቻ፣ የመራመድ እና የአጥንት መሰበር ሊያጋጥማቸው ይችላል። እንደነዚህ አይነት ችግሮች ሲገጥማቸው በብዛት ወደ ጤና ተቋም የመሄድ አዝማሚያው ከፍ ያለ ነው።

‎ይሁን እንጂ በእድሜ መግፋት ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎች መካከል የመርሳት ወይም የመዘንጋት ችግር ሲያጋጥም፣ ወደ ጤና ተቋም የመሄድ ዝንባሌው ዝቅተኛ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በነርቭ ህክምና ክፍል ውስጥ መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር ያሬድ ዘነበ፣ ‎ከሚያረጁ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ አንጎል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። ‎በአንድ ግለሰብ አንጎል ውስጥ በአማካይ ከ80 እስከ መቶ ቢሊየን የነርቭ ህዋሶች ተዋቅረው እንደሚሰሩ ይገልፃሉ።

‎እነዚህ ህዋሶች አንዱ ከሌላው ጋር ለመናበብ የኤሌክትሪክ ንግግር እንደሚያደርጉም ነው ዶክተር ያሬድ ያስረዱት።

‎ይህንን ንግግር ለማድረግ በትሪሊየን የሚቆጠር መልዕክት ይላላካሉ ያሉት ዶክተር ያሬድ፣ በልጅነት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጀምሮ ጎልማሳ እስኪሆን ድረስ፣ አእምሮ በተለያዩ መንገዶች እራሱን እያሳደገ እንደሚመጣ ያስረዳሉ። አንጎል በዋናነት በሁለት መንገድ እንደየምንጠቀመው የገለጹት ባለሙያው፣ አንደኛው ከከባቢ የሚመጡ መልዕክቶችን መተርጎም መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ይህም አንጎል በራስ ቅል ውስጥ የሚቀመጥ በመሆኑ፣ በዙሪያው የሚከናወነውን ነገር የሚያውቀው ወይም የሚረዳው በአምስቱ የስሜት ህዋሳት እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከውስጥ አካላችን ጋር ከልብ፣ ከአንጀት እና ከመሳሰሉት ጋር መልዕክት ለአንጎል ይደርሰዋል ብለዋል።

‎የተቀበለውን ወይም የደረሰውን መልዕክት ከበፊት ትውስታ ጋር በማጣመር፣ በማወዳደር አዲስ ትውስታ በመፍጠር ደግሞ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ‎ይህ ማለት ጡንቻን ያዛል፣ ሰውነትን እንዲንቀሳቀስ፣ ለወደፊት እንዲያቅድ እና እንዲሰራ ያደርጋል በማለትም አስገንዝበዋል።

‎ይህንን የማድረግ ችሎታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሲሄድ፣ በተለምዶ እርጅና መሆኑን በብዙዎች ሲነገር እንደሚስተዋል አንስተዋል።

የመርሳት በሽታ ምልክቶቹ ምንድናቸው?

‎የአልዛይመር በሽታ ምልክቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ በሽታ ነው።

አንድ ሰው ነገሮችን ለማስታወስ እና አዲስ እውቀት ለመቅሰም መቸገር፣ ዕቃዎችን ማጣት፣ ዝግጅቶች ወይም ቀጠሮዎች መርሳት ያሉት ‎የማስታወስ ችሎታ ከማጣት ምልክቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

‎ከዚህ በተጨማሪ ገንዘብ ወይም ሂሳቦች የመክፈል ችግር፣ ስለ ደህንነት እና አደጋዎች ግንዛቤ መቀነስ፣ እንደ ልብስ መልበስ ያሉ በርካታ ደረጃዎች ያሉት ተግባራትን የማጠናቀቅ ችግር የዚህ በሽታ ምልክቶች ናቸው።

‎ከበፊቱ በበለጠ መበሳጨት፣ መናደድ ወይም መጨነቅ፣ ግዴታ አለመወጣት፣ ለሚወዷቸው ተግባራት ፍላጎት ወይም ተነሳሽነት ማጣት ሌላኛው ምልክቶች ናቸው።

‎እንደዚህ አይነት ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሰዎች ወደ ህክምና በማምራት ህመሙን በመለየት፣ መንስኤው ከታወቀ በማከም፣ የማይታከም ከሆነ ደግሞ እንዳይባባስ ስሜቱን በመቆጣጠር ታማሚውና ቤተሰቦቻቸውን መርዳት አንደሚቻል ነው የገለፁት።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review