ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ቀጣይነት ከተረጋገጠ በ5 ዓመታት ውስጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይቻላል

You are currently viewing ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ቀጣይነት ከተረጋገጠ በ5 ዓመታት ውስጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይቻላል

AMN- ህዳር 3/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ቀጣይነት ከተረጋገጠ በ5 ዓመት ውስጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል በዓለም አቀፍ የምግብ ምርምር ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ እና የማህበራዊ ጤና ተመራማሪ ታደሠ ዘርፉ (ዶ/ር) ገለጹ።

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ገና ያልተሻገሩት በምግብ ራስን መቻል ጉዳይ አሁንም አጀንዳ ከመሆን ያለመሻገሩን ያነሱት ዶክተር ታደሠ፣ የሠው ልጅ በምግብ ውስጥ በሚፈጠር የብረት ወይም አዮዲን እጥረት አንድ ሦስተኛውን የማሰብ ችሎታ ይዘት (አይ ኪው) ሊያጣ እንደሚችል ገልፀዋል።

ከኤ ኤም ኤን 96.3 ሬዲዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ተመራማሪው፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት በሥርዓተ ምግብና በምግብ ራስን መቻል ላይ እየሠራ ያለው ተግባር ተስፋ ሰጭ መሆኑን አንስተው፣ በተከታታይ መስራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ የበለፀጉ የሚባሉት እንደነ ቻይና፣ ህንድ፣ ኔዘርላንድስ እና የመሳሰሉት ሀገራት በምግብ እጦት ተቸግረው እንደሚያውቁ በማጣቀሻ ያነሱት ዶክተር ታደሠ፣ ኢትዮጵያ አሁን በያዘችው እቅድ ከቀጠለች ችግሩ በአምስት ዓመታት ውስጥ ታሪክ መሆን ይችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የውሃ ሃብት ለመስኖና ለመሳሰሉት የልማት ሥራ ከ10 በመቶ ያልዘለለ መሆኑን በማንሳትም፣ የውሃ አጠቃቅምን በፍጥነት ለመጨመር ተገቢው ጊዜ መሆኑን አስምረውበታል።

በጣም ትንሽ መሬት እና የሰው ሀብት ያላቸው ሀገራት ግብርናው ላይ የሚታይ ለውጥ ያመጡት በተማረ የሰው ሃይል እና በዘመናዊ መንገድ መሆኑን ያነሱት ተመራማሪው፣ በዚህ ረደግ ኢትዮጵያ እምቅ ሀብት ስላላት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥነውን የምግብ አጀንዳ ዘግቶ ሌሎች የፈጠራ አጀንዳዎችን ማቀድና መተግባር ይገባል ብለዋል፡፡

በሲሳይ ንብረቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review