የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ረገድ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት አለበት

You are currently viewing የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ረገድ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት አለበት

AMN- ህዳር 4/2018 ዓ/ም

አንድ ሀገር፣ ሀገር ሆኖ ለመቆም እና ዕውቅና ሊኖረው ካስፈለገ ድንበር፣ መንግስት እና ሉዓላዊነት ሊኖሩት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ሀገር ደግሞ ያለ ብሔራዊ ጥቅም ምንም እንደመሆኗ መጠን፣ ለሀገራት መቀጠል ብሔራዊ ጥቅሞቻቸው የሚጫወተው ሚና ትልቅ ነው፡፡

ለዘመናት ተፈጥሮ በቸራት ሀብት በሚፈለገዉ መጠን መጠቀም ሳትችል የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ከጉያዋ ሲሸሽና ሌሎችን ሲያበለጽግ የቆየው የዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገንብታ ፊቱን ወደ ቤቱ እንዲመልስ በማድረግ ይቻላልን ለዓለም አሳይታለች፡፡

ዛሬ ደግሞ ይህንን ጥንካሬዋን ይዛ ትኩረቷን ወደ ሌላኛው የህልውናዋ መሰረት ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር ላይ አድርጋለች፡፡

ለኢትዮጵያ የጊዜው ወሳኝ ጉዳይ የባህር በር መሆኑን ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ጥቅም ስለአንድ ነገር ብቻ ሳይሆን፣ የሀገርን ብልጽግናን እና ሰላማዊ ጉዞ የሚያረጋግጡ ወሳኝ ጉዳዮችን መያዙን የሚያነሱት ምሁራኑ፣ ብሔራዊ ጥቅምን በአግባቡ ያለመረዳት ውጤት የሆኑ ተግባራት እንደሚስተዋሉ ይጠቁማሉ፡፡

የቀድሞ የኦነግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢብሳ ነጋዎ፣ በኢትዮጵያ የምግብ ደህንነት መረጋገጥ በራሱ አንዱ ብሔራዊ ጥቅም ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

ዜጎች በልተው ማደር፣ ልጆችን ማስተማር እና ሌሎችም የሚጠበቅባቸውን ቤተሰባዊና ሀገራዊ ኃላፊነቶች መወጣት እንዲችሉ የምግብ ደህንነት መረጋገጥ አለበት በማለትም አክለዋል፡፡

ይህንን ያልተረዳ ደግሞ ጠብመንጃ አንስቶ ለሌሎች የውክልና ጦርነት ውስጥ ይገባል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

የዓባይ ንጉሶች ሚዲያ ባለቤት ኡስታዝ ጀማል በሽር በበኩላቸው፣ ያልተሰሩ የቤት ሥራዎች እንዳሉ በመጥቀስ፣ አንድን ነገር ለመውደድም ሆነ ለዛ ጉዳይ ወታደር ሆኖ ለመነሳት በጉዳዩ ላይ ጥሩ እውቀትና መረጃ ሊኖር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ብሔራዊ ጥቅም የአንድ ግለሰብ ወይም የአንድ መንግስት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ በማንሳትም፣ እነዚህን የጋራ ጉዳዮች ለማስጠበቅ፣ ካለፈው ትምህርት መውሰድ እንደሚያስፈልግና ክፍተት ያለባቸውን አካሄዶች ማረም አንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ጥሩ አስተማሪ እንደሆነ ያነሱት ኡስታዝ ጀማል፣ ከአፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ በመንግስታት ቅብብሎሽ የመጣውን ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተረክበው አስጨርሰው ለፍፃሜ ማድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም አንድ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ሰዎች ተቀባብለው መስራታቸውን በማመላከት፣ በሀገራዊ ጉዳይ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በርዕዮተ ዓለም በመሳሰሉት መስማማት ግድ አለመሆኑን ያሳያል ሲሉም አክለዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ምሁር አቶ ጥላሁን ሊበን፣ ብሔራዊ ጥቅም የሚሳካው በመጀመሪያ እንደሀገር ሀገራዊ አንድነትን በመፍጠር እና ሰላምን በመፍጠር የራሳችንን የቤት ሥራ በመስራት ነው ብለዋል፡፡

ህዝቡም ብሔራዊ ጥቅሙን ለማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት ካላቸው ተቋማት ጎን መቆም እና በጋራ መስራት እንዳለበትም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review