የተራ አስከባሪ እና የፓርኪንግ ማህበራት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል

You are currently viewing የተራ አስከባሪ እና የፓርኪንግ ማህበራት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል

AMN – ህዳር 5/2018 ዓ.ም

የተራ አስከባሪ እና የፓርኪንግ ማህበራት የከተማዋን ዕድገት የሚመጥን እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለፀ፡፡

የቢሮው የሕዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ከፓርኪንግና ከተራ አስከባሪዎች ማህበራት አመራሮች ጋር በተርሚናሎች እና በተሽከርካሪ ማቆሚያ አካባቢዎች ምቹ አገልግሎት መስጠትን ያለመ ውይይት እየተካሄደ ነው ።

በውይይቱ ላይ ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉትን የአገልግሎት ክፍያ በእጅ የሚሰበሰብ የተራ አስከባሪ እና የፓርኪንግ ማህበራት ወደ ዲጂታል ስርዓት መግባት ግዴታ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍስሃ ጥበቡ ገልጸዋል ።

የትራስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ምሽት ላይ ከታሪፍ በላይ ክፍያ ማስከፈል አሁንም የሚስተዋል ችግር በመሆኑ ይህንን ለመፍታት ከተራ ማስከበር እና ከፓርኪንግ ማህበራት ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠበቅ ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል ።

የተራ አስከባሪ እና የፓርኪንግ ማህበራት የከተማዋን ዕድገት የሚመጥን እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል ።

የአገልግሎት መስጫ ተርሚናሎች እና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች ምቹ ፣ ጽዱና ድህነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን መትጋት እንደሚገባቸው በውይይት መድረኩ ተገልጿል ።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉትን የአገልግሎት ክፍያ ታሪፍ 10 ብር ዝቅተኛ በመሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግበት ሲሉ ጠይቀዋል ።

ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉትን የአገልግሎት ክፍያ በዲጂታል ክፍያ የመሰብሰብ ስርዓት ላይ የክህሎት ክፍተት በመኖሩ ለመፍትሔው በጋራ መስራት አለብንም ብለዋል።

ቢሮው በተርሚናሎች እና በተሽከርካሪ ማቆሚያ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቀነስ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ጠቅሶ የውይይቱ ተሳታፊዎች ያነሷቸው ጥያቄዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል ተብሏል ።

ማህበራቱ በከተማዋ ያለውን ሰላም በማጽናት ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና አጠናክንረው እንዲቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍስሃ ጥበቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዳንኤል መላኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review