በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለቤትነት የተሠራው “ስለእናት ምድር” የተሰኘው ታሪካዊ ፊልም በአፍሪካ የፊልም አካዳሚክ አዋርድ (AMAA) በምርጥ የቪዡዋል ኢፌክት ዘርፍ ተሸላሚ ሆነ።
ፊልሙ “የአፍሪካው ኦስካር” እየተባለ በሚጠራው ታላቅ የሽልማት መድረክ ላይ ከ500 ፊልሞች መካከል በ8 ዘርፎች ታጭቶ የታጨ ሲሆን፤ በአንዱ ዘርፍ ሽልማት ማግኘቱ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረበት የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ተሾመ ለኤኤምኤን ዲጂታል ተናግሯል።

“ስለእናት ምድር” በዘንድሮው AMAA አዋርድ ላይ ታጭቶ የነበረው በምርጥ ጽሑፈ ተውኔት፣ ኤዲቲንግ፣ ዳይሬክተር፣ ምርጥ ወንድና ሴት ተዋናይ፣ ምርጥ ቪዥዋል ኢፌክትና ሲኒማቶግራፊ፣ እንዲሁም በምርጥ ፊልም ዘርፎች ነው።
ደራሲና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ፊልሙ ከሁሉም ሥራዎቹ የላቀ መሆኑን ገልፆ፤ በፊልሙ የተነሳ ጥይት ተተኩሶብኝ ተርፌያለሁ ሲል ገልጿል፡፡
ባሳለፍነው ሕዳር 30/2018 በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ በተካሄደው የሽልማት ሥነ ስርዓት ላይ ከመሪ ተዋናዮቹ ጋር በአካል ተገኝቶ ሽልማቱን የተቀበለው ቴዎድሮስ ተሾመ፤ “ስለእናት ምድር” ከዚህ ቀደም ከሠራቸው “ቀዝቃዛ ወላፈን”፣ “ፍቅር ሲፈርድ”፣ “ቀይ ስሕተት” እና “አባይ ወይስ ቬጋስ” ሁሉ የሚበልጥ መሆኑን ከኤኤምኤን ዲጂታል ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
“ፊልሙ ከሁሉም ሥራዎቼ የላቀው ነው”

ፊልሙ 3 ሰዓታት የሚረዝም ሲሆን ከ30 ሺህ በላይ ተዋንያንም ተሳትፈውበታል። መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በሀገር ውስጥ በምርቃት መልክ ቢታይም እስካሁን ድረስ ለሕዝብ ክፍት አልሆነም ብሏል።
በተቀራራቢ ጊዜ በሀገረ አሜሪካ ሎስ አንጀለስ በተካሄደ የፊልም ፌስቲቫል ላይም ከሁለት መቶ ፊልሞች መካከል ተመርጦ በመክፈቻው ዕለት ለዕይታ በቅቶ የበርካታ ሽልማቶች ባለቤት መሆን ችሏል።
በፊልሙ የተነሳ በግል ሕይወቴ ተፈትኛለሁ
በፊልሙ የተነሳ በግል ሕይወቴ ተፈትኛለሁ የሚለው ዳይሬክተሩ፤ የፊልሙን 20 በመቶ ያህል በጀት በወሰደው በቪዥዋል ኢፌክት ዘርፍ ተሸላሚ መሆኑ እንዲሁም በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ስም መጠራቱ ታላቅ ደስታና ክብርን እንደፈጠረለት ተናግሯል።

በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ላይ መሠረት ያደረገውን ይህንን ፊልም በመሥራቱ የተነሳ በግል ሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ስድብ፣ ወከባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ በማሕበራዊ ትስስር ገጾች ይደርሰው እንደነበር ለኤኤምኤን ዲጂታል ተናግሯል።
በዚህ የተነሳ ልጆቹን ከሀገር እስከማሸሽ የደረሰ ሲሆን አንድ ቀን በድንገት በተተኮሰብኝ ጥይት ከሞት ለጥቂት ነው ያመለጥኩትም ብሏል።
በዚህ ጦርነት ያሸነፈችውም የተሸነፈችውም ኢትዮጵያ ናት የሚል ጭብጥ ባለው በዚህ ፊልም ብዙ ውጣ ውረድ ያሳለፈው ቴዎድሮስ ተሾመ ይህን ሽልማት በማግኘቱ፣ በመድረኩ ላይ የተወዳጁን ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ “ኢትዮጵያ የእኛ መመኪያ” የተሰኘውን ሙዚቃ ለመጫወት በመቻሉና የመድረክ አጋፋሪዋ ስለኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ስኬቶች በልበ ሙሉነት እንድትናገር ምክንያት በመሆኑ ከፍተኛ ኩራት እና ክብር እንደተሰማው ገልጿል፡፡፡