በመታመን የተገኘ ክብር

You are currently viewing በመታመን የተገኘ ክብር

   • ለታማኝ ግብር ከፋዮች የተዘጋጀ ልዩ የተጠቃሚነት ዕድል መኖሩ ተመላክቷል

አቶ ሰዒድ ሀሰን፤ የሀስ ኢንተርፕራይዝ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ድርጅታቸው የተመሰረተው ከ20 ዓመት በፊት ሲሆን፤ ሥራውን የጀመረው ብረታብረት በማስመጣት እና በማከፋፈል ነበር፡፡ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ እና ከውጭ ሀገር የሚገቡ የብረት ምርቶችን (ቱቦላሬ፣ ሺት ሜታሎች፣ ላሜራዎች…) በማስመጣት በግንባታ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያከፋፍላል፡፡ ተደራሽነቱም ሙሉ የኢትዮጵያ ክፍል ነው።ሀስ ኢንተርፕራይዝ ባሳለፋቸው ሁለት አስርት ዓመታት ዕድሜ ውስጥ ውጤታማነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ያስታወሱት አቶ ሰዒድ፤ “አሁን ላይ በዋናው የሀስ ኢንተርፕራይዝ ስር የተለያዩ እህት ድርጅቶችን አቋቁመን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ በሲዳማ ክልል በ1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በመስኖ እርሻ ልማት ተሰማርተናል፡፡ ዓለም ገና ላይ የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ድርጅት አለን። ለትንባሆ ሞኖፖል ድርጅት ግብዓት የሚያቀርብ የትንባሆ ማቀነባበሪያ (የቶባኮ ፕሮሰሲንግ) ፋብሪካ አለን። ከዚህ በተጨማሪም በቤቶች ግንባታ ላይ የተሰማራ የሪልስቴት ድርጅትም ወደ ሥራ አስገብተናል” በማለት ያብራራሉ፡፡ የሀስ ኢንተርፕራይዝ እና እህት ድርጅቶቹ ከ300 በላይ ቋሚ እንዲሁም ከ600 በላይ ጊዜያዊ  የሥራ ዕድል ለዜጎች መፍጠር መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

በሥራ የሚያምኑት፣ ሠርቶ መለወጥን በተግባር ያረጋገጡት፣ ከራሳቸው አልፎ ለትውልድ እና ለሀገር የሚጠቅሙ ድርጅቶችን በማቋቋምና ለውጤት በማብቃት ምሳሌ የሆኑት የሀስ ኢንተርፕራይዝ መስራች አና ሥራ አስኪያጅ፤ ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈልም የተመሰከረላቸው ናቸው። ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ “ግብር ለሀገር ክብር!” በሚል መሪ ሐሳብ ባሰናዳው የታማኝ ግብር ከፋዮች የዕውቅና ሽልማት መርሃ ግብር  ላይ የፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ከሆኑት መካከል የሀስ ኢንተርፕራይዝ አንዱ መሆኑ ለዚህ ምስክር ነው፡፡

“የንግድ ፍቃዳችንም፣ ግብር የምንከፍለውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ነው፡፡ ይህንን ዕውቅናና ሽልማት ስናገኝ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም፡፡ አምናም በተመሳሳይ የፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ነበርን” የሚሉት አቶ ሰዒድ ለሽልማት ያበቃቸውን ልምድ እና አሠራር እንደሚከተለው አብራርተዋል፤ “ለሽልማት ያበቃን የከፈልነው የግብር መጠን፣ በደረሰኝ ሽያጭ ወይም ግብይት ማድረግ ዋናው መመዘኛ ነው፡፡ እኛ ምንም ዓይነት ግብይት ያለደረሰኝ አናከናውንም፡፡ ሽያጭን በደረሰኝ ማከናወን የድርጅታችን ባህል ነው፡፡ ይህም የገቢዎች ተቋም የክትትል ሠራተኞች ወደ ድርጅታችን መጥተው በሚያደርጉት ክትትልና ቁጥጥር ለማረጋገጥ የቻሉት ሀቅ ነው፡፡ ‘የእኛ የእኛ፤ የመንግስት የመንግስት ነው፡፡’ የሚል መርህ በድርጅታችን በወጥነት ይተገበራል፡፡ ማንኛውም ሠራተኛ ወደ ድርጅቱ ሲቀጠር ቀድሞ ስለ ድርጅቱ የሥራ ባህል በቂ ግንዛቤ ይፈጠርለታል። መብትና ኃላፊነቱን እንዲያውቅ ይደረጋል። በመዘናጋትም ይሁን ሆን ተብሎ ያለ ደረሰኝ የሚፈፀም ግብይት ካለ፤ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊነት የሚወስደው በወቅቱ ለችግሩ መፈጠር ምክንያት የሆነው ሠራተኛ ነው፡፡”

ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ በተሰናዳው እና በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተከናወነው የታማኝ ግብር ከፋዮች የዕውቅና ሽልማት መርሃ ግብር ላይ የሀስ ኢንተርፕራይዝን ጨምሮ 387 ግብር ከፋዮች ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የህግ ተገዥነት ጥናትና ስትራቴጂ ዝግጅት ቡድን አስተባባሪ አቶ ወንድወሠን ጥላሁን በበኩላቸው ግብር ሲከፈል ሀገር ታድጋለች፤ ግብር ከፋዮች ደግሞ ግዴታቸውን በመወጣታቸው መብታቸውን የመጠየቅ ሞራል እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

የሀስ ኢንተርፕራይዝ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ  ሰዒድ የራሳቸውን ልምድ በማከል ሀሳቡን ያጠናክራሉ፡፡ ይህንንም፤ “ድርጅታችን በዓመት እስከ 200 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የግብር ገቢ ለመንግሥት ይከፍላል፡፡ በወቅቱ ነው የምንከፍለው፡፡ ይህንን ገንዘብ ስንከፍል የተለየ ነገር እንዳደረግን አንቆጥረውም፡፡ ምክንያቱም አንድ ግብር ከፋይ ግብር የሚከፍለው ካተረፈው ውስጥ የራሱን ድርሻ በማስቀረት እና ለመንግስት ተብሎ የተቀመጠውን ድርሻ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተሰብስቦ ዜጎች በጋራ ሊጠቀሙባቸው ለሚችሉ የልማት ሥራዎች የሚውል ነው” በማለት ገልጸውታል፡፡ ድርጅታቸው ግብር ከመክፈል ባለፈ፤ በከተማ አስተዳደሩ በተካሄዱ የልማት እና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ ነው፡፡ ለአብነት በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብ እና መሰል ድጋፍ ማድረጉ፣ ለዚህ ተግባሩም ዕውቅናና ሽልማት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የዩናብ ቢዝነስ ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በፕላቲኒየም ደረጃ ዕውቅናና ሽልማት ከተሰጣቸው ድርጅቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ የዩናብ ቢዝነስ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. የፕላቲኒየም ደረጃ ሽልማትን ለ4ኛ ጊዜ እንዳገኘ የድርጅቱ ዳይሬክተር ዮናታን ዐቢይ፤  በታማኝነት የሚከፍሉት ግብር ልማት ላይ እየዋለ መሆኑን በአዲስ አበባ በተሰሩ የልማት ሥራዎች ማረጋገጣቸውን እና በዚህም ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

“የግብር ከፋዮችን የህግ ተገዥነት ደረጃቸውን በመለካት የተሻለ የህግ ተገዢነት ደረጃ ያላቸውን እውቅና መስጠት እና ማበረታታት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመምታትን ያክል ድርብ ዓላማዎችን የሚያሳካ መሆኑን የጠቀሱት በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የህግ ተገዥነት ጥናትና ስትራቴጂ ዝግጅት ቡድን አስተባባሪ አቶ ወንድወሠን፤ ይህም ለህግ ተገዥ ያልሆኑ ግብር ከፋዮች ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር የህግ ተገዢነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለውጤት ለማብቃት አቅም ይፈጥራል፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደር የታዩ ስኬቶችን ዘርዝረዋል፡፡  የግብር ከፋዮች የታክስ ግዴታን በራስ ተነሳሽነት የመወጣት አቅም ማደጉን፣ በየጊዜው የሚጠበቀውን ገቢ መሰብሰቡን፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት መሰጠቱን፣ ለህግ ማስከበር እና የግብር ገቢን ለመሰብሰብ የሚወጡ ወጪዎችን መቀነሱን፣ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያስችሉ አቅሞችን መፍጠሩን፣ በግብር ከፋዩ እና በግብር ሰብሳቢው መካከል ጤናማ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር ማድረጉን እንዲሁም በህዝብ በኩል የተቋሙ ተዓማኒነት እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለማቋረጥ እየተተገበረ ያለው የታማኝ ግብር ከፋዮች የዕውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር ለታማኝ ግብር ከፋዮች በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደሚሰጥ ተሸላሚዎቹ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለጋዜጣችን ሐሳብ እና አስተያየታቸውን የሰጡት የሀስ ኢንተርፕራይዝ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰዒድ፤ “ለታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅናና ሽልማት መሰጠቱ፤ የድርጅት ባለቤቶች ‘ለካ መንግስት መልካም ተግባራችንን ይመለከታል’ እንዲሉ ያደርጋል፡፡ ለተሻለ ሥራ ያነቃቃል። ለታማኝነት፣ ለመልካም ሥምና ዝና መጠበቅ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጥ ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም፤ ለታማኝ ግብር ከፋዮች የቪአይፒ አገልግሎት ማግኛ ዕድልን ያስገኛል፡፡ እኔም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚገኘው አገልግሎት ቅድሚያ እንዲሰጠኝ የሚያስችል የቪአይፒ መጠቀሚያ ካርድ ተሰጥቶኛል፡፡ በዚህም በገቢዎች ቢሮ የሚሰጠውን አገልግሎት በቅድሚያ እና በፍጥነት ማግኘት ችያለሁ። ጅምሩ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡” ብለዋል፡፡ 

ለታማኝ ግብር ከፋዮች እንደከተማ አስተዳደር የተዘጋጀ ልዩ የተጠቃሚነት ዕድል መኖሩን ያነሱት በገቢዎች ቢሮ የህግ ተገዥነት ጥናትና ስትራቴጂ ዝግጅት ቡድን አስተባባሪው፤ ለተሸላሚዎች በዕለቱ ከሚሰጠው ዕውቅና በተጨማሪ በቢሮው የተዘጋጀ የአገልግሎት ቅድሚያ ማግኛ መታወቂያ እና ሰርተፊኬት እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በፕላቲኒየም እና በወርቅ ደረጃ ለተሸለሙ ግብር ከፋዮች በከተማ አስተዳደሩ በማንኛውም አገልግሎት የቪአይፒ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የታማኝ ግብር ከፋዮች የዕውቅናና ሽልማት መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ለሀገር የታመኑ ግብር ከፋዮችን ለማበረታታት በፕላቲየም ደረጃ ዕውቅና እና ሽልማት ለተበረከተላቸው ድርጅት ባለቤቶች ወይም ሥራ አስፈጻሚዎች ዓለማቀፍ ሥራቸውን ቀላል ያደርግላቸው ዘንድ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንደሚሰጣቸው መግለፃቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር፤ ለ245 በወርቅ ደረጃ ተሸላሚዎች ደግሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቪአይፒ ተርሚናል መጠቀም እንደሚችሉ አብስረዋል፡፡ በቀጣይም የታማኝ ግብር ከፋዮች ቁጥር ከዘንድሮውም በበለጠ በብዙ አድጎ እንደሚመለከቱ ተስፋቸውን ጠቁመዋል። ለዚህም ስኬት ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review