ስዕል ጥንታዊ ከሆኑ የኪነጥበብ ዘርፎች መካከል አንደኛው ነው፡፡
ስዕል ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ የሰዎች አኗኗር እንዲሁም የሰዓሊው ውስጣዊ ሀሳብ እና ዓለምን የሚመለከትበት መንገድ ይንጸባረቃል፡፡
ወጣት ሽፈራው ፍቅሬ ይባላል አካል ጉዳተኛ ቢሆንም፣ ጉዳቱን ወደ ቀለም ስሜቱን ደግሞ ወደ ጥበብ በመቀየር ስዕሉን ለሚመለከቱ ሁሉ ተስፋን፣ ብርታትን እና ወኔን የሚያላብስና የሚያጋባ ወጣት ነው፡፡

ወደ ስዕል መሳል ሥራ ከገባ 7 ዓመታትን አስቆጥሯል፤ ስዕል መሳል ከገቢ ማግኛነቱ በተጨማሪ፣ ተስፋ ላለመቁረጥ የሚያበረታ ደስ የሚል ስሜት እንዳለው ይናገራል፡፡
የስዕል ሥራዎቹን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ በመልቀቅ እንደሚያስተዋውቅ የሚገልጸው ወጣት ሽፈራው፣ የተከታዮቹን ቁጥርም ከፍ እያደረገ መምጣቱን ይናገራል፡፡
የአካል ጉዳቱ የተከሰተው እድሜው 18 ዓመት ከሞላ በኋላ መሆኑን የሚያነሳው ሰዓሊው፣ ቢሆንም ለጉዳቱ እጅ ባለመስጠት የስዕል ሥራውን አጠንክሮ በመያዝ ውጤት እያስመዘገበ ስለመሆኑ ይገልፃል፡፡

የስዕል ሥራ ውስጥ መግባቱ በብዙ መልኩ ህይወቱን እንደለወጠው በመናገርም፣ ወጣቶች በሚችሉት ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ በትንሹ በመንቀሳቀስ እራሳቸውን ከአላስፈላጊ ጭንቅት እና መሰል ችግሮች እንዲጠብቁ ይመክራል፡፡
ሰዓሊ ሽፈራው ወደፊት ሥራውን በማሳደግ የራሱን የስዕል ማሳያ (ጋለሪ) የመክፈት እና የማሰልጠኛ ማዕከል የማቋቋም ህልም እንዳለውም ያወጋል፡፡
ሰዓሊ ሽፈራው እሱን ማግኘት ለሚፈልጉ (ሽፌ አርት) በሚል በፈጠረው የቴሌግራም ግሩፕ እና ቲክቶክ ገጹ ሥራዎቹን እንደሚያቀርብም ተናግሯል፡፡
በታምራት ቢሻው