የአፍሪካ ህብረት እና ኢትዮጵያ በቀጣናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስን(ዶ/ር) ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሊቀ መንበሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተለዋዋጭ በሆነው የቀጣናው ምህዳርና የአፍሪካ ህብረትና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ግጭትን በመከላከል ዲፕሎማሲ (preventive diplomacy)፣ ግጭትን ማስቀረት፣ ሰብዓዊ ምላሽ እና ዘላቂ ልማት ላይ ያላቸውን ማዕከላዊ ሚና አስመልክቶ ተወያይተዋል።
ሁለቱ ባለስልጣናት እየተባበሰ የመጣው የሱዳን ጉዳይ እጅጉን እንደሚያሳስባቸው ገልጸው በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የደቡብ ሱዳን ጉዳይን በተመለተም ሁሉም የደቡብ ሱዳን ተዋንያን እ.አ.አ በ2018 በአዲስ መልክ በተፈረመው የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ እንዲያከብሩ እና የፖለቲካ መረጋጋት እንዲሰፍን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በሳሄል ቀጣና ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ባለስልጣናቱ ኢ-ህገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጥ የተደረገባቸው ሀገራት ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት በፍጥነት የሚመለሱበትን ግልጽ እና ተአማኒነት ያላቸው ፍኖተ ካርታዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን የአፍሪካ ህብረትን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
የአፍሪካ ህብረት እና ኢትዮጵያ በቀጣናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰሩም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።