ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያን ቁልፍ የትኩረት መስኮች ባማከለ መልኩ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታወቁ።
የአፍሪካ የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ፎረም በሞሮኮ ራባት ተካሄዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ሲዲ ኡልድ ታህ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የበጀት ድጋፍን ማጠናከር፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ጨምሮ በሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የተቀናጀ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር ማድረግ እና ኢትዮጵያ የምታዘጋጀውን 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በፋይናንስ መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ያላቸው የቆየ አጋርነትም በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ባንኩ ለኢትዮጵያ የልማት ስራዎች እየተወጣ ያለውን ወሳኝ ሚናም አንስተዋል።
ባንኩ የኢትዮጵያን ግዙፍ ፕሮጀክቶች በፋይናንስ ለመደገፍ ያለውን ዝግጁነት አድንቀዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት ሲዲ ኡልድ ታህ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የሪፎርም ሂደት ያደነቁ ሲሆን ባንኩ በኢትዮጵያ የግል ኢንቨስትመንትን በሚያሳድጉ እና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት በሚፈጥሩ መስኮች ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ እና የባንኩ ፕሬዝዳንት በውይይቱ ላይ ተከታታይና የቴክኒክ ምክክሮችን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ አጋርነታቸውን በዘላቂ ልማት፣ ቀጣናዊ ትስስር እና የግሉ ዘርፍ እድገት በሚያጠናክር መልኩ ለማጎልበት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኤኤምኤን በላከው መረጃ አመልክቷል።