AMN – የካቲት 4/2018 ዓ.ም
የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ተሳታፊዎችን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ሆቴሎች ገለጹ፡፡
39ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ይካሄዳል፡፡ የህብረቱ ሥራ አስፈጻሚዎች ውይይትም ዛሬ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጉባኤውን ለመታደም በርካታ እንግዶች ወደ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም ይመጣሉ፡፡ የሚመጡትን እንግዶች በላቀ ሁኔታ ለማስተናገድ ዝግጀት ማድረጋቸውን ኤ.ኤም.ኤን ያነጋገራቸው ሆቴሎች ገልጸዋል፡፡
የኔክሰስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለልዑል ይልማ፣ እንግዶችን በተሻለ ሁኔታ ለማስተናገድ እንዲያስችላቸው በሆቴላቸው እድሳት ማድረጋቸውን ተናገረዋል፡፡
ለአፍሪካዊያንና ከሌላ የዓለም ክፍል የሚመጡ እንግዶች የሚሆኑ የምግብ ዝግጅት ማድረጋቸውንና ኢትዮጵያዊ ባህልን ለማስተዋወቅም የባሕል አዳራሽ በልዩ ሁኔታ መሰናዳቱን አስታውቀዋል፡፡
ለእንግዶቹ የሚያስደስት መስተንግዶ ለመስጠት ለሠራተኞቻቸው ሥልጠና መስጠታቸውን የገለጹት ደግሞ የክራይሰንት ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስረስ ድፌ ናቸው፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም ከአየር ማረፊያ ጀምሮ ኢትዮጵያን በሚያስተዋውቅ ሁኔታ እንግዶቻቸውን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ እጅግ ውብ ሆናለች ያሉት ሥራ አስኪያጆቹ ፣ በከተማዋ አጫጭር ጉዞችን በማዘጋጀት ለማስጎብኘት መዘጋጀታውን ተናግረዋል፡፡
የሆቴል ባለንብረቶች ማሕበር ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አስቴር ዮሐንስ የአፍሪካዊያን የኩራት ምንጭ የሆነችው አዲስ አበባ፣ እያሳየች ያለውን ለውጥና እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ ታሪካዊ ሥፍራዎችን ለማስጎብኘት ዝግጅት መደረጉንና ለሆቴሎችም ጥሩ የሥራ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢኒያም ታዬ በበኩላቸው፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በከተማ እንግዶችን ለማስተናገድ የሚችሉ 40 ያህል ሆቴሎች መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለዩት ሆቴሎችም ለሠራተኞች፣ በደንበኛ አቀባበልና አያያዝ ሥልጠናዎች መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ለሚመጡት እንግዶች አዲስ አበባን እንዲጎበኙ ከጉዞ ወኪሎች ጋር በመነጋገር የጉብኝት ጥቅል መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በታደሰ ሽፈራው