AMN – የካቲት 5 ፣ 2018
የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እንዲቀጣጠል ምክንያት የሆነው የዓድዋ ድል በተለያዩ ሀገራት እንዲከበር እና በዓለም የታሪክ ትምህርት ውስጥ ሰፊ ቦታ እንዲኖረው በጋራ መሥራት እንደሚገባ የታሪክ ምሁራን ገለጹ።
“የዓድዋ ትሩፋት ለዛሬዋ ኢትዮጵያ እና ለነገው ትውልድ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጉባዔ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የታሪክ ተመራማሪውና የቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አበባው አያሌው (ረ/ፕ)፣ የዓድዋ ትውልድ ለጥቁር የሰው ልጆች ሁሉ የነጻነት ቀንዲል መሆን አንደቻለ ተናግረዋል።
ይህ ትውልድ የራሱን ታሪክ በራሱ ቀለም መጻፍ ከፈለገ የዓድዋን መርሕ ሊከተል እንደሚገባው ያነሱት የታሪክ ተመራማሪው ድሉን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
ማንኛውንም ነገር ለማሸነፍ በጋራ መቆም የግድ መሆኑን ከዓድዋ በላይ ምስክር እንደሌለ የጠቀሱት ደግሞ ሌላው ጽሑፍ አቅራቢ አሻግሬ ገ/ብረወልድ (ዶ/ር) ናቸው።
የፓን አፍሪካኒዝም የነጻነት ንቅናቄ እንዲቀጣጠል ምክንያት የሆነው የአድዋ ድል የዓለምን ሥርዓት ዳግም የበየነ ታላቅ ክስተት መሆኑን ነው አሻግሬ ገ/ብረወልድ የጠቀሱት፡፡
የዓድዋ ድል የሀገርን ሉዓላዊነት ያጸና ወታደራዊ ድል ብቻ ሳይሆን ማኀዕበራዊ አምዶችን ያጎለበተ ዓለም አቀፍ ክስተት መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።
በካሳሁን አንዱዓለም