AMN- ጥቅምት 1/2019 ዓ.ም

ፈርዖኖቹ ኢትዮጵያን እንደ ህልውና ስጋታቸው የሚመለከቷት ከተሳሳተና ተጨባጭ ካልሆነ እሳቤ መሆኑን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ዋንኛው የፈርዖኖቹ ስጋት የሚመነጨው ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ ይህም አሁን ላይ ምንም አይነት ህጋዊ ተቀባይነት የሌለውን የቅኝ ገዢዎች ስምምነትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡
አባይ ከአጠቃላይ የናይል ወንዝ ፍሰት ወደ 85 በመቶ የሚጠጋውን የሚያበረክት ቢሆንም፣ ግብጽ ግን የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የመጠቀም ታሪካዊ መብት አለኝ ብላ በተሳሳተ መረጃ ላይ ቆማ ኢትዮጵያን ትከሳለች፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን የልማት እና የኃይል ፍላጎት ማሟላት እና ውሃውን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም ህጋዊ መብት ያላት።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሀገራት በዉሃዉ የመጠቀም መብት ቢኖራቸዉም ግብጽና ሱዳን ግን የቅኝ ግዛት ውሎችን በመጠቀም ለረጅም ዘመናት ዉሃውን በብቸኝነት ሲጠቀሙበት ኖረዋል።
ፈርዖኖቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምታደርጋቸው ማናቸውም የልማት ስራዎች የውሃ መጠኑን ሊቀንስብን ይችላል ብለው የሚሰጉት ከተጨባጭ መረጃ ተነስተዉ ሳይሆን ሆን ብለዉ የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር መሆኑን ምሁራን ያስረዳሉ።
ስጋቱ የሚመነጨው ኢትዮጵያ የአባይን ዉሃ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመጠቀሟ ምክንያት ሳይሆን፣ ዉሃውን በብቸኝነት ለመጠቀም ካላቸው ስግብግብ ፍላጎት ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ በፍትሃዊ የዉሃ አጠቃቀም መርህ በጋራ የመጠቀም እንጂ ጎረቤት ሀገራትን የመጉዳት ምንም ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ አሳዉቃለች።
ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ገንብታ ቀጣናውን በኃይል በማስተሳሰሯ የተጠቀመ እንጂ የተጎዳ ጎረቤት ሀገር አለመኖሩ ደግሞ የፈርዖኖች ስጋት መሰረተ ቢስ እና በሴራ የታጀበ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ፈርዖኖቹ ምንም አይነት ህጋዊ ተቀባይነት በሌለው ማስረጃ፣ ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም አቀፍ መድረኮች ደጋግመው ቢከሷትም ተቀባይነት እና ሰሚ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
ይልቁንም አፍሪካ ብሎም የተቀረው ዓለም ከቅኝ ግዛት ነፃ በወጣበት በዚህ ዘመን፣ ግብጽ ወደ ኋላ ተመልሳ ይህንን ጥያቄ ማንሳቷ ዉሃውን ለብቻዋ ለመጠቀም ያላትን ስግብግብ ፍላጎት አጋልጦባታል።
ፈርዖኖቹ ተጨባጭ ባልሆነ ምክንያት ስጋት አለብን ብለዉ ኢትዮጵያን የሚከሱት በቀጣናው የበላይነት ለመውሰድ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ መሆኑንም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ፈርዖኖቹ ኤርትራን ጨምሮ ከአንዳንድ የጎረቤት ሀገራት ጋር ጥምረት ፈጥረው በቀጣናው የበላይ ሆነው ለመታየት የሚሞክሩትም በሀገራቱ መካከል ጤናማና ህዝቦቻቸውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ስላላቸው አይደለም፡፡
ይልቁንም በሴራ፣ በደባና በተንኮል ላይ በተመሰረተ ግንኙነት ኢትዮጵያን በተለያዩ መንገዶች አዳክመው በቀጣናው የበላይ ሆነው ለመታየት ካላቸው ስግብግብ ፍላጎት እንጂ፡፡
ለዚህም ነው ፈርዖኖቹ ሻዕቢያን፣ ህገወጡ የህወሃት ቡድንና ጽምዶን የመሰሉ ጽንፈኛ ኃይሎችን ከጀርባ ሆነው እየደገፉ ኢትዮጵያን ለዘመናት ሲፈታተኑ የኖሩት፡፡
ኢትዮጵያ በሻዕቢያና በህገወጡ ህወሃት ተላላኪነት ለረጅም ዘመናት ስትጠቀምበት የነበረውን የባህር በር በግፍ ተነጥቃ ዛሬ ላይ የጂኦግራፊ እስረኛ የሆነችዉም በፈርዖኖቹ ድብቅ ሴራ ነዉ።
ይህም የኤርትራንና የትግራይን ህዝብ ለመጥቀም ሳይሆን፣ የፈርዖኖቹን ስግብግብ ፍላጎት ለማሟላት ታቅዶ መሆኑን ያረጋግጣል።
ፈርዖኖቹ እነዚህንና መሰል ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በተለያዩ የዓለም መድረኮች በኢትዮጵያ ላይ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን፣ ስም የማጥፋት ዘመቻዎችንና ክሶችን ቢያቀርቡም ዓለም ሊሰማቸው አልፈቀደም፡፡
ይልቁንም ኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ ያጣችውን የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በአፍሪካና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ ለፈርዖኖቹ ሌላ ስጋት እና መርዶ ሆኗል፡፡
ፈርዖኖቹ እንደ ሻዕቢያ እና ህገወጡ ህወሃት ያሉ ቋሚ ቅጥረኞችን በመጠቀም ቀጣናውን ለመክበብ እና ጫና ውስጥ ለማስገባት ቢሞክሩም፣ ኢትዮጵያ የገነባችው ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት ይህንን ስግብግብ ፍላጎታቸውን እንዲፈጽሙ የሚፈቅድ ሆኖ አልተገኘም፡፡
ከለዉጡ ወዲህ በልዩ ትኩረት የተገነባው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን፣ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት በብቃት መጠበቅና ማረጋገጥ የሚችል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በውስጥ የሚልኳቸውን ባንዳዎች በጀግንነት እየመከተ የሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ አሁን ላይ በተለያዩ ግዳጆች ላይ እያሳየ ያለው የመፈጸም አቅም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውና ለአፍሪካም ጨምር ትልቅ ተስፋና መተማመኛ ሆኗል፡፡
ይህም የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ትልቅ ስጋት ዉስጥ ከቷቸዋል።
በወንድማገኝ አሰፋ