AMN መስከረም 15/2019
ታዋቂዉ የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ አቀንቃኝ አርቲስት ዳዊት መኮንን ከ27 ዓመታት የዉጭ ሃገር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
በፊንጫአ ከተማ ተወልዶ ያደገው ዳዊት በ1980ዎቹ ውስጥ ‘ሶላኔ’፣ ‘ፈርደ ጉራቻ’ እና ሌሎችንም የፍቅር እና የትግል ሙዚቃዎችን በማዜም ይታወቃል፡፡
አርቲስት ዳዊት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ‘አን ዱፌን ጅራ’ የተሰኘ አልበም በማሳተምም ከፍተኛ ተደማጭነትን አትርፏል።
አርቲስት ዳዊት መኮንን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲደርስ የነበረውን በደል በኪነ-ጥበብ ይታገል ስለነበር ለደህንነቱ ሲል ሀገሩን ጥሎ ወደ ውጭ ሀገር ለመሰደድ ተገዷል፡፡
አርቲስት ዳዊት እንደሌሎቹ የኦሮሞ ታጋዮች እና ዘፋኞች በለውጥ አመራሩ ያገኘዉን መብት ተከትሎ ከ27 ዓመታት በኋላ ዛሬ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
አርቲስት ዳዊት መኮንን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን አመራሮች፤ አባገዳዎች፤ የጥበብ ባለሙያዎች እና ሌሎች እንግዶች ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።