ህዝብን በቅንነት ለማገልገል የተጀመሩ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያማከሉ አሰራሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

ህዝብን በቅንነት ለማገልገልና የሚነሱ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት የተጀመሩ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያማከሉ አሰራሮች በይበልጥ ተስፋፍተው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩን የ1ኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ማጠቃለያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ከተማ አስተዳደሩ ህዝብን በቅንነት ለማገልገልና የሚነሱ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት የተጀመሩ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያማከሉ አሰራሮች በይበልጥ ተስፋፍተው እንደሚቀጥሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በዚህም በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚዘጋጁት እንደ “አገልጋዩ” እና “ዋርካ” ያሉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ለአስተዳደሩ ግልጽነት፣ ለህዝብ ጠያቂነት እንዲሁም ለሚነሱ ጉዳዮች ምላሽ ሰጪነት መጎልበት ያደረጉት ጥረት በጥንካሬ የሚታይና ሊሰፋ የሚገባው መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጠናቀቀው ሩብ ዓመት ከሕዝብ የቀረቡ ከ495 በላይ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች 495ቱ መፍትሔ ማግኘታቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ተጠያቂነትን ለማስፈን በተደረገው ጥረት፣ 95 የሚሆኑ አመራሮችና ሠራተኞች በሥራ አፈጻጸም ጉድለት ምክንያት ተጠያቂ መደረጋቸውንም ነው የገለጹት።

ከብልሹ አሰራርና ሙስና ጋር በተያያዘም ከ90 በላይ አመራሮች፣ ሠራተኞች እንዲሁም ተገልጋዮችን ጨምሮ በሕግ ተጠያቂ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review