የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት አይቀሬ ነው

AMN – ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ የባህር በር አልባ በመሆኗ በውጭ ንግድ እና በኢኮኖሚ ዕድገቷ ላይ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች።

ሀገሪቱ የባህር በር ማግኘቷ እንደ ሕልውና ጉዳይ የሚታይ ሲሆን፣ ከጂኦፖለቲካዊና ከኢኮኖሚ አንፃርም ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡

ኢትዮጵያ ለአብዛኛው የውጭ ንግዷ ከ95 በመቶ በላይ በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ መሆኗ፣ ከፍተኛ የወደብ ክፍያ፣ የትራንስፖርት፣ የወደብ ኪራይ፣ የማጓጓዣ እና የማከማቻ ወጪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምሩ አድርጓል።

አሰብ እና ምጽዋ ከኢትዮጵያ እጅ መውጣታቸው ሀገሪቱን በዓለም ላይ በሕዝብ ብዛት ትልቋ የባህር በር የሌላት ሀገር አድርጓታል።

ብዙ ኢትዮጵያውያን ይህ ሂደት ብሔራዊ ጥቅሟን ያላስከበረ አግባብነት የሌለው ውሳኔ እንደነበር ይገልጹታል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ፣ ቀይ ባህርን መጠቀም የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ አይቀሬ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ የወደፊት ዕድገት እና ሥልጣኔ ያለ ባህር በር ሙሉ ሊሆን ስለማይችል፣ የባህር በር ማግኘት ከምንም ነገር በላይ ቀዳሚው እና ወሳኙ ጉዳይ ነው።

ይህንን የባህር በር ፍላጎት በሰላማዊ ውይይት፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በባለቤትነት መጋራት መርህ ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል።

ለቀጣይ ስትራቴጂካዊ ዝግጅቶች ሲባልም፣ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል እንደገና ተቋቁሟል።

ኢትዮጵያ ያጣቸውን ሀብት መልሳ ለማግኘት የምታደርገውን ሰላማዊ ጥረት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተረድቶ ድጋፉን እያሳየ መጥቷል፡፡

አካሄዱም ዓለም አቀፍ ሕግን ያከበረና ለጋራ ተጠቃሚነት የቆመ መሆኑ ግልፅ ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የንግድ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ እና የውጭ ንግድ ሎጂስቲክስ ሰንሰለቷን አስተማማኝ ለማድረግ፣ የወደብ አማራጮቿን የማስፋት እና መሠረተ ልማቶችን የማጠናከር ሥራዎቿን በማጎልበት መቀጠል ይኖርባታል።

ሕዝቡ የባህር በር ፍላጎት የፖለቲካ፣ የብሔር ወይም የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር የሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሕልውናና የጋራ ጥቅም የሚያስጠብቅ አጀንዳ መሆኑን ተገንዝቦ በአንድነት መቆም ይገባዋል።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ ዜጎች በሚኖሩበት ማኅበረሰብና በሚኖሯቸው ግንኙነቶች ውስጥ የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት ፍትሃዊነትና ሕጋዊ መሠረት በማስተዋወቅ የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review