AMN – ጥቅምት 7/2019 ዓ.ም
አዲስ አበባን የስፖርት ቱሪዝም እና የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎ፣ መዲናዋን የአህጉሩ የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህንን ያሉት በ16ኛው የአዲስ አበባ ስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
በመልዕክታቸውም፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና ወጣቶች ያላቸውን ከፍተኛ የስፖርት ፍቅር በመገንዘብ፣ አስተዳደሩ የሕዝቡን ፍላጎት ከመንግሥት የልማት አቅጣጫዎች ጋር በማጣጣም በተግባር ምላሽ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ስፖርት ለመዝናናት እና ለውድድር ብቻ የሚውል ሳይሆን፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን የሚያጠናክር፣ የሕዝብ አንድነትን፣ ወዳጅነትንና ፍቅርን የሚገነባ ትልቅ መሣሪያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ የስፖርት ቱሪዝም ዋነኛ መዳረሻ ለማድረግ የታቀደው ራዕይ ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም፣ ስፖርት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክርና በሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት የሚያጎለብት ውጤታማ የዲፕሎማሲ መድረክ በመሆኑ፣ ዘርፉን ማሳደግ ዘለቄታዊ ጥቅም እንደሚያስገኝ ነው የገለጹት።
ከንቲባዋ አክለውም፣ የስፖርት አፍቃሪው ማኅበረሰብና ባለሙያዎች በዘርፉ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ እና ሰፊ ዕድል እንዲያገኙ የተጀመረው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በተመለከተም፣ ግንባታዎቹ አካታች በሆነ መልኩ በየአካባቢውና በየሰፈሩ ለወጣቱ ቀርበው እንዲስፋፉ መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የከተማዋ መንገዶች ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆኑና የእግር መንገድ ባህል እንዲጎለብት መደረጉ ከጤና እና ከማኅበራዊ መስተጋብር አንፃር አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ለስፖርት ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ያነሱት ከንቲባዋ፣ የተመዘገቡ ስኬቶችን መነሻ በማድረግ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠልና የበለጠ ውጤታማ ማድረግ የሁሉንም የጋራ ኃላፊነት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!