የግብር ከፋዮች የእውቅና እና ሽልማት ስርዓት ዓላማ

You are currently viewing የግብር ከፋዮች የእውቅና እና ሽልማት ስርዓት ዓላማ

AMN -ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም

የ6ኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና እና ሽልማት ሥነ-ስርዓት በትናንትናው እለት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ተካሒዷል፡፡

በዚሁ ፕሮግራም ላይ 550 ግብር ከፋዮች እውቅና እና ሽልማት ያገኙ ሲሆን ግብር ከፋዮች በሀገር ውስጥ ገቢ በ12 እና በጉምሩክ በ7 የመምረጫ መስፈርቶች መሰረት ተመዝነው እውቅናው ተሰጥቷቸዋል፡፡

ለመሆኑ የግብር ከፋዮች የሕግ ተገዥነት ማለት እና የግብር ከፋዮች የእውቅና እና ሽልማት ስርዓት ዓላማ ምንድነው ፡-

ግብር ለአንድ ሀገር አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው እድገት አንዱ መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን ኢኮኖሚው ሊያመነጭ የሚችለውን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ ግብርን በፈቃደኝነት የመክፈል ባህልን ማሳደግና የግብር ከፋዮችን የህግ ተገዥነት ሁኔታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም በተቋሙ የግብር ከፋዮች የህግ ተገዥነትን ለማሣደግ ከተቀረጹት ስትራቴጂዎች ውስጥ ከተመላከቱ ስልቶች መካከል በህግ ተገዥነታቸው እና ለገቢው ባደረጉት አስተዋጽኦ የተሻሉ ግብር ከፋዮችን እውቅናና ሽልማት መስጠት ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህም ስራ ከ2011 በጀት ዓመት ተጀምሮ እየተከናወነ የመጣ ሲሆን ዘንድሮ ለ6ተኛ ጊዜ ተከናውኗል፡፡

ዓላማውም በዋናነት በአገር ውስጥ ታክስ እና በወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ የአሰራር ስርዓቶችን እና ህጎችን አክብረው ግብር የከፈሉትን ግብር ከፋዮች ማበረታታት እንዲሁም የታክስና ቀረጥ የአሰራር ስርዓቶችን እና ህጎችን የማያከብሩና የሚጠበቅባቸውን ግብር የማይከፍሉ ከዚህ ትምህርትና ተሞክሮ በመውሰድ ወደ ትክክለኛው የታከስ አሰራርና ህግ ማክበር እንዲገቡ ለማድረግ ነው፡፡

በዚህ ደረጃ ለእውቅና እና ሽልማት የሚለዩ ግብር ከፋዮች በተቀመጠላቸው ዝርዝር የመመዘኛ መስፈርቶች የሚታዩ ሲሆን ዋና የትኩረት አቅጣጫዎቹ 2 ናቸው እነሱም፡-

1. ግብር ከፋዮች በአገር ውስጥ ታክስ እና በወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ የአሰራር ስርዓቶችና ህጎች ላይ ያላቸው ታማኝነት

2. በበጀት ዓመቱ ግብር ከፋዮች ለገቢው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል ከነበረው በዚህ ዓመት በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ተጠቅሞ ግብርን የማስታወቅ፣ የመክፈልና ከተቋሙ ጋር በስርዓቱ ተገቢውን ግንኙነት የማድረግ ሁኔታ የመምረጫ መስፈርቱ አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ የህግ ተገዥነት ማለት ለተለያዩ ህጐች፣ መርህዎች እና መለኪያዎች መገዛት፣ መታዘዝ፣ መስማማት ማለት ሲሆን እነዚህ ህጐች እና መመሪያዎች የወጡበት ዓላማ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ማድረግ ማለት ነው፡፡

የታክስ ህግ ተገዥነት ማለት ደግሞ መንግስታት የታክስ ገቢን ለመሰብሰብ ያወጡትን የታክስ ህጎችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን እና መርሆዎችን በፈቃደኝነት በማክበር የግብር እና ቀረጥ ግዴታዎችን በተገቢው ጊዜ እና በተገቢው መንገድ መወጣት ማለት ነው፡፡

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እያንዳንዱ የታክስ አስተዳደር ከግብር ከፋዮቹ የሚጠብቀው 4 መሠረታዊ የህግ ተገዢነት ግዴታዎች ያሉት ሲሆን እነዚህም፡-

1. በግብር ከፋይነት መመዝገብና ለውጦችን ማስመዝገብ /Registration and notify the change /፣

2. ግብርን በወቅቱና በትክክል ማሳወቅ /Filing/፣

3. በወቅቱ ለቀረበ ማስታወቂያ ትክክለኛነት ማረጋገጥ ወይም ትክክለኛ ደጋፊ ማስረጃዎች ማቅረብ እና አስፈላጊ ለሆነው ጊዜ መያዝ /Reporting/፣

4. ግብርን በወቅቱ መክፈል /On time payment/ መሆናቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review