ብሪክስ እ.ኤ.አ በ2006 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መስራች ሀገራት ይፋ ባልሆነ መልኩ ተጀመረ። ከ3 ዓመት በኋላ ማለትም 2009 ዓ.ም አባል ሀገራቱ ይፋዊ ስብሰባቸውን አድርገዋል፡፡ ብሪክስ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ከፍ ማድረጊያ መሳሪያ እና በአለም አቀፍ አስተዳደር ላይ ሚዛን ለመጠበቅ ያለመ ነው ተብሎ ይነገራል። አባል ሀገራቱ ከዓለም ህዝብ 45 በመቶውን ይሸፍናሉ። 28 በመቶ የሚጠጋውንም የአለም ኢኮኖሚም ይይዛሉ ይላል ዘኢኮኖሚስት ሰሞኑን የብሪክስ አባል ሀገራት እና የዓለም መሪዎች በሩሲያ፣ ካዛን ኤክስፖ ማዕከል ያደረጉትን ስብሰባ አስመልክቶ ያስነበበው መረጃ፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አባል ሀገራቱ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነትም ከአለማችን የህዝብ ቁጥር አብዛኛውን ህዝብ ይዘዋል፡፡ ከአለም ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ሦስት በመቶውን ይሸፍናሉ…፡፡ በመሆኑም ብሪክስ እኩልነት የነገሰባትን አለም ለመፍጠር ትልቅ አቅም አለው። ስለሆነም በብዙ ኢኮኖሚያዊና መሰል መስኮች በጋራ አብረን መስራት ይኖርብናል፡፡ ህብረቱ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ፍላጎት ለማሟላትም ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።

በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀገሪቱ እምቅ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብት እንዳላትና ለአብነትም በቅርብ አመታት ውስጥ ማህበረሰቡን በማስተባበር በአረንጓዴ አሸራ መርሃ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል መቻሉን፣ በስንዴ ምርት ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ እስከማቅረብ መደረሱን እና መሰል ሀገራዊ ስኬቶችን አንስተዋል፡፡
እንደ ሀገር በስኬት የሚገለፅ ልዩ ልዩ ተግባራት እንዳሉ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነትም በስማርት ሲቲ፣ በከተማ ግንባታ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና መሰል የልማት ዘርፎች በሀገሪቱ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመጥቀስ አባል ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሙሐመድ አማን ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፣ ብሪክስ ሲመሰረት የራሱ የሆነ አላማ ይዞ ነው። ሀገራቱም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም አላቸው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከህብረቱ አባል ሀገራት ጋር ያላትን ሀብት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ብትንቀሳቀስ የበለጠ ዕድገቷን የሚያፋጥን ዕድል አላት ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር መሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው መሳተፋቸው ሀገሪቷ ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንድትሆን በር የሚከፍት ነው ያሉት መምህሩ፣ ለአብነትም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እስካሁን ከሌሎች ሀገራት ጋር የምትሰራቸው የተለያዩ ልማቶች አሉ፡፡ ከብሪክስ አባል ሀገራት አንፃር ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትን እና መሰል ሀገራትን ብናይ ግብርና ላይ እንዳይሰሩ የሚያደርጋቸው ትልቁ ችግር ውሃ የላቸውም፤ እኛ ውሃው አለን፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሀገራት ግብርና ላይ ኢንቨስት ማድረግ ከፈለጉ ሀገራቸው ላይ ስለማይችሉ አባል ሀገራቱ ግብርናን ሲያስቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ዕድል ይፈጠራል፡፡
በመሆኑም ይላሉ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ግብርና ላይ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የምንሰራበት ዕድል ካለ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ለዚህ የሚመች መሬት አላት፡፡ በመሆኑም ሩሲያን ከመሳሰሉ ስንዴ አምራች ሀገራት ጋር በጋራ በመስራት የበለጠ መጠቀም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ብራዚልን ብንወስድ የህብረቱ አንዱ አባል ናት፡፡ ብራዚል ደግሞ ከአለማችን አሉ ከተባሉ የቡና አቅራቢዎች መካከል አንዷ በመሆኗ ከብራዚል ጋር በቡና ዘርፍ አብረን መስራትና የበለጠ መለወጥ እንችላለን፡፡
ስለሆነም ይላሉ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ የብሪክስ አባል ሆንን ማለት፣ ከእያንዳንዱ አባል ሀገራት ጋር የተለያየ አይነት ግንኙነት ይኖረናል። ለምሳሌ በቡና መስራት ከፈልግን እንደ ብራዚል ካሉት ጋር ልምድ እንለዋወጣለን፤ አብረንም እንሰራለን፡፡ እንስሳት ላይ የሚሰሩ ካሉ ከእነርሱ ጋር ደግሞ አብረን እንሰራለን፡፡ በመሆኑም ትልቁ ነገር በየትኛው ዘርፍ ከየትኛው ሀገር እጠቀማለሁ የሚለው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው እና መሰል ዘርፎች እንዳለን ሀብት እና እንደ ሀገራቱ ሁኔታ አንፃር በየዘርፉ የምንጠቀምበት ዕድል ይኖራል፡፡ ከዚህ ዕድል የበለጠ ለመጠቀም በየዘርፉ ያሉ ተቋማት የራሳቸው ጥንካሬና ጥረት ሊኖር እንደሚገባ የጠቆሙት መምህሩ፣ ለዚህ ደግሞ ከእያንዳንዱ አባል ሀገራት ጋር የተለያየ ስትራቴጂ መንደፍ ያስፈልጋል፤ ምን ሰጥቼ ምን አገኛለሁ? የሚለውን ማስላት ይገባልም ብለዋል መምህሩ፡፡
እንደ አፍሪካ ዜና አገልግሎት ዘገባ፣ ኢትዮጵያ የቡድኑ አባል መሆኗ አለም አቀፋዊ ገፅታዋን እንደሚያሳድግ፣ ከአንዳንድ ታላላቅ የአለም ኃያላን መንግስታት ጋር እንድትገናኝ እና የበለጠ ተቀራርባ እንድትሰራ እና ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያስችላታል። የህብረቱ አባል መሆኗ ሀገሪቱን በጂኦ ስትራቴጂያዊ ደረጃ ተጠቃሚ ያደርጋታል የሚለው ዘገባው ለአብነትም ኢትዮጵያ በዓመት በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች አንዷ መሆኗን እና ወደ ህብረቱ መቀላቀሏ ደግሞ ይህንን ከፍታዋን እንደሚያፀናው ጠቅሷል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ ከቻይና ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ፈጥራለች። በተመሳሳይ የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው፡፡ ቻይና እና ህንድ ደግሞ የአፍሪካ ሁለት ትልልቅ የንግድ አጋሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም ከእነዚህና ከሌሎቹም የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የበለጠ በልማትና በሌሎች ዘርፎችም በመስራት ዕድገቷን ማፋጠን ያስችላታል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር በመሆኗ በጂኦ ፖለቲካዊ ዘርፍ ከምታገኘው ጠቀሜታዎች በተጨማሪ፣ የላቀ ቴክኖሎጂን፣ ፈጠራን እና የእውቀት ልውውጥን የሚያመጣ አጋርነትን ያጎለብታል፤ ይህም ኢትዮጵያ በግብርና፣ ኢነርጂ እና ትምህርት በመሳሰሉት ወሳኝ ዘርፎች እንድታድግ ይረዳታል። ለአብነትም ኢትዮጵያ በኢነርጂ ዙሪያ እንደ ሩሲያ ካሉ በዘርፉ ትልቅ ደረጃ ከደረሱት አገራት ጋር በመሥራት ጉልህ ለውጥ እንደምታመጣም ተጠቅሷል፡፡
የሀገራቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ጥቅል ምርት 16 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት መሆኑና ይህም ከዓለም አቀፍ ዓመታዊ ጥቅል ምርት ስሌት 23 በመቶ የሚጠጋውን የሚሸፍን መሆኑ ብሪክስን ከወዲሁ ተፈላጊ እና የሚነገርለት ማኅበር አድርጎታል። ብሪክስ ለአባል ሀገራቱ መሰረተ ልማት ድጋፍ የሚያደርግ የራሱ የሆነ ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ያለው መሆኑ እና በጥቂት ኃያላን ሀገራት የሚዘወረውን የዓለም ሚዛን ማስጠበቅ ላይ የሚሠራ እንደሆነም ዘገባዎቹ ያመላክታሉ። ይህን ማኅበር ለመቀላቀል ብዙ ሀገራት በይፋም በድብቅም ጥያቄዎቻቸውን አቅርበው እየተጠባበቁ መሆኑም እየተነገረ ነው።
የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ብሪክስን እንደ አንድ የፋይናንስ ምንጭነት መጠቀም አስፈላጊ ነው። ብሪክስ አባል ሀገራቱ የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ድጋፍ የሚያደርግ በመሆኑም ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በተያያዘም ብሪክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር የሚሠራ ተቋም በመሆኑ ተፈላጊነቱ እየጨመረ እንደመጣም ይነገራል፡፡
“ብሪክስን መቀላቀል ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ምን ያስገኛል?” ሲል ቢቢሲ በቅርቡ የሰራው ዘገባ እንደሚያመለክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ቡድኑን የተቀላቀለችው በታሪኳ፣ በሕዝብ ብዛቷ በተለይ ደግሞ በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ስለታመነበት እና የመደመጥ አቅሟም እያደገ በመምጣቱ ነው። በመሆኑም ይህ ዕድል ምጣኔ ሃብታዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሞችን እንድታገኝ ያስችላታል ይላል ዘገባው፡፡
የፈጣን አዳጊ አገሮች ማኅበር እየተባለ የሚጠራው ብሪክስ፣ ለአባል ሀገራቱ ብዙ ጥቅሞችም እንዳለው ይነገራል፡፡ ምክንያቱም የብሪክስ አገሮች ጉልህ የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው እንዲሁም ቴክኖሎጂያዊ አቅምን በሚገባ የፈጠሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 70 ሚሊዮን ሔክታር የሚታረስ መሬት አላት፡፡ በግብርና ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ቴክኖሎጂ ለማግኘት ሰፊ እድልን እንደሚፈጥርላትም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ማኅበር፣ “የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ምን ያስገኝላታል? እይታና ዓለም አቀፍ አዝማሚያ” ሲል ባደረገው ጥናት ላይ እንደተመላከተው፣ ብሪክስ ከተመሰረተባቸው ሰባት ዓላማዎች ውስጥ አንዱ እንደ ዓለም አቀፍ ንግድ ያሉ ጥቅሞችን ማግኘት ነው፡፡ ይህንን ለማግኘት ደግሞ የኢትዮጵያ የቤት ስራ ከፍተኛ ነው። ንግድ ወይም ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ከተባለ እነሱ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በደንብ ሊሰሩ የሚችሉበት እድል መኖር አለበት። የንግድ ስርዓቱ በጣም የተሻለ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ የገንዘብ ስርዓት፣ የገንዘብ ገበያ እድገት የመሳሰሉት በሙሉ ከብሪክስ አባላት ጋር እንዲጣጣሙ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል፡፡
የብሪክስ ህብረት የዓለማችን ታላላቅ የሃይል አምራቾችን እና ገዢዎችን በአንድ ላይ የማሰባሰብ አቅም ያለው ነው፡፡ የንግድ መረቦች፣ የፋይናንስ አማራጮች፣ የገንዘብ ፖሊሲዎች፣ የቴክኖሎጂ ትብብር፣ የመሠረተ ልማት ዕድገት ለማፋጠን ትልቅ አቅም አለው ይላል መረጃው፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ይፋ ያደረገው የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የብሪክስ አባል ሀገራት በአፍሪካ በ2015 ከ500 ቢሊዮን ዶላር በላይ የንግድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ የብሪክስ ህብረት በአፍሪካ፣ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ እና በአገልግሎት ዘርፍ ሰፊ ድጋፍ እያደረገ ነው። በተለይም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ ለውጥ መጥቷል ብሏል፡፡
እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ ከሆነ የብሪክስ ሀገራት በአፍሪካ ውስጥ እንዲሳተፉ ካደረጋቸው ምክንያቶች መካከል በአህጉሪቱ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ የአፍሪካ ሰፊ እና ያልታረሰ የግብርና መሬት፣ ብዙ እና አዳዲስ የገበያ አማራጮች እንዲሁም ኢንቨስት ለማድረግ እና የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግር በተሳካ መልኩ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ስላለ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው እምቅ የተፈትሮ ሀብት፣ የመልማት አቅም፣ ሊያሰሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችን በተለይም በቅርቡ ወደ ሙሉ ተግባራዊ ምዕራፍ የተሸጋገረው የኢኮኖሚ ሪፎርም የብሪክስ አባል ሀገራት ከሀገሪቱ ጋር በተለያዩ የዕድገት ዘርፎች ላይ የበለጠ እንዲሰሩ ምቹ መደላድል ስለመሆኑም የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናገራሉ፡፡
በመለሰ ተሰጋ