የገጠር አካባቢዎች የበለፀጉ ባህል፣ ቅርስ እና ጥልቅ ማህበራዊ ትስስር ያላቸው ደማቅ የሀገሪቷ ክፍሎች ናቸው። ካላቸው የተትረፈረፈ ፀጋ አንፃር ሲመዘኑ ተፈጥሮ ልግስናዋን የጀመረችባቸው ስፍራዎችም ይመስላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ…
“እስኪ ገጠር ልሒድ ከለምለሙ ስፍራ፣
መላ ሰውነቴ በሐሴት ይሞላ።
ወተቱ ከማጀት እሸቱ ከጓሮ፣
በጣም ያስደንቃል የገጠሩ ኑሮ…”
እያልን በስንኝ ቋጠሮ ብንሸፋፍነውም ብዙ የገጠር ስፍራዎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ፣ የሰለጠነ የአኗኗር ዘይቤ እና የበለፀገ መንገድን የሚከተሉ ባለመሆናቸው ከምቾት እንደራቁ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

ለአብነትም እውቁ እንግሊዛዊ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሮበርት ጆን ሃይሎክ “Rural Development: Putting the Last First” የተሰኘ ድንቅ የምርምር መፅሀፍ አላቸው፡፡ በዚህ የምርምር ስራቸው እንደገለፁት፣ የገጠር ድህነት፣ ኑሮና ሁኔታ ብዙውን ጊዜ በውጭ ሰዎች በወጉ የማይታይ ወይም የተዛባ ግምት የተሰጠው ነው። ይህም በመሆኑ የገጠር አካባቢዎች በቀላሉ ሊስተካከሉ በሚችሉ ችግሮች ወይም አስተሳሰቦች ምክንያት የድህነት መገለጫ ሆነዋል ይላሉ፡፡
በመሆኑም የገጠር ብልጽግና ለሀገር ልማት ያለውን ጠቀሜታ በወጉ በመገንዘብ መስራት የሀገርን ከፍታ በፅኑ መሰረት ላይ ማንበር የሚያስችል ድንቅ ጥበብ ነው፡፡ በገጠር ብልጽግና ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ በገጠር የሚኖሩ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች መፍታት ብቻ ሳይሆን ከተማውንም ማሳደግ በጥቅሉም የሀገርን ብልፅግና ባስተማማኝ መልኩ ማረጋገጥ ስለመሆኑም ፀሐፊው በጥናታዊ መፅሐፋቸው ያትታሉ፡፡
ይህንን እውነት በመገንዘብም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በኢትዮጵያ የገጠር ኮሪደር የተሰኘ መርሃ ግብር ተጀምሯል፡፡ የገጠር ኮሪደር የገጠሩን ህይወት፣ ጤና፣ የአኗኗር ዘይቤውን ዘመናዊ በማድረግ፣ የበለፀገ አኗኗርን በማምጣት፣ የገጠሩ ነዋሪ ባለው ሀብት ልክ ምቹ ኑሮ እንዲኖር ከማስቻል አንፃር ያለው ፋይዳ እጅግ የገዘፈ ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሟላ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንዲቻል፣ ሕይወትን በቤተሰብ ደረጃ መቀየር የሚያስችሉ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል፡፡ ለአብነት አረንጓዴ ዐሻራ፣ በምግብ እህል እራስን መቻል፣ የሌማት ትሩፋት፣ የኮሪደር ልማት እና መሰል የልማት መርሃ ግብሮች ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ ተሸጋግረው ከቤተሰብ ተጠቃሚነት አለፍ ያለ ውጤትም እያስመዘገቡ ነው፡፡ የእነዚህ ስራዎች አላማም ሰብዓዊ ልዕልናን ማረጋገጥ እንደሆነ መንግስት ይፋ አድርጓል፡፡
በአሁኑ ሰዓት አርሶ አደሮች እርሻቸውን በኩታ ገጠም በማረስ ምርታቸውን ጨምሮ ገቢያቸውም እያደገ ነው፡፡ የገቢ ማደግ ብቻ አኗኗርን አዘምኖ ለመጭው ዘመን ስለማያዘጋጅ በከተሞች እንደተጀመረው ሁሉ በገጠርም የኮሪደር ልማት ስራ አስፈላጊ መሆኑንም መንግስት አሳውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የገጠር ኮሪደርን አስመልክቶ ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክታቸው እንደጠቀሱት፣ የገጠር ኮሪደር ማለት የእያንዳንዱን አርሶ አደር ቤት የአኗኗር ዘዬ መቀየር ማለት ነው፡፡ ፅንሰ ሀሳቡን ሲያብራሩም፣ “አንዱ አርሶ አደር በጓሮው እንሰት፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ዶሮ፣ ሁለት ሦስት የሚታለቡ ላሞች ካሉት ሀብታም ነው። ይህ ሀብታም ግን ለሀብታም የተገባ ኑሮ እንዲኖር፣ ከመንገድ ገባ ብሎ ቤቱን እንዲሰራ፣ አጥሩን በቀርቀሃና በአረንጓዴ እፅዋት እንዲያጥር ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፣ የዚህ መርሃ ግብር ዋናው አላማ በቤተሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር ነው፡፡ ምክንያቱም የገጠሩ ነዋሪ የአኗኗር ዘዬው ካልተቀየረ በስተቀር በሀገር ደረጃ የሚታሰበውን ብልፅግና ማረጋገጥ አይቻልም። የለማ ሀገር መፍጠር የሚቻለው ከቤተሰብ የሚጀምር ሁለንተናዊ ልማትን ማረጋገጥ ሲቻል እንደሆነ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለአብነትም በቤተሰብ ደረጃ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ባለው ሀብትና ፀጋ ልክ እንዲበለፅግ እና በዚያው ልክ ሕይወቱን እንዲመራ ጣልቃ መግባት ያስፈልጋል፡፡
የገጠር ኮሪደር መርሃ ግብር ጉዳይን አስመልክቶ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጀማ ሐጂ፣ በገጠሩ ክፍል በደንብ ገባ ብሎና ያላቸውን ሀብት ተረድቶ በቤተሰብ ደረጃ መስራት ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ገጠሩ የማህበረሰብ ክፍል ቀረብ ብሎ ያላቸውን ሀብት፣ የትምህርት ደረጃ፣ የመሬት ስፋት፣ የቤተሰቡ አቅም እና መሰል ነገሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህንን ሀብታቸውን ምን ምን ላይ ቢያውሉ የተሻለ ምርታማ ይሆናሉ? ባላቸው ሀብት ልክስ እንዴት ሊኖሩ ይገባል? የሚለውን ማመቻቸትና መንግስትም ደከም በሚሉበት ቦታ ድጋፍ ከሰጠ ምርታማነት ያድጋል፤ ይህ ማለት ደግሞ የሀገር ዕድገት በአስተማማኝ መልኩ እንዲረጋገጥ ያግዛል፡፡
ከምርታማነትም ባሻገር የገጠሩ ማህበረሰብ ባለው ሀብት ልክ ምቹ ኑሮ እንዲኖር ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይህም ከቤተሰብ ምጣኔ ጀምሮ መሰራት ያለበት እንደሆነም ጠቅሰዋል። ይህም ባለው ሀብት መጠን ያለመኖርን ችግር ይቀርፋል። ባለ ሀብት ልክ ያለመሆን ችግር እንደ ሀገር በስፋት የሚስተዋል እንደሆነ አንስተው፣ ለአብነትም ቤተሰብን በአግባቡ አለማስተዳደር በተለይም ልጆችን ተመጣጣኝ ምግብ እየሰጡ ያለማሳደግ ክፍተት አለ፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ትልቅ ሸክምን ይፈጥራል፡፡ ኢትዮጵያ በልጅነት ወቅት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት ምክንያት ወደ 16 ነጥብ 5 በመቶ አምራች ኃይሎች ታጣለች። ይህም በቤተሰብ ደረጃ ብዙ ስራዎች እንደ ሀገር መስራት እንዳለብን ያመላክታል ብለዋል፡፡
ባለው ሀብት ልክ የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ እንዳለ ሆኖ የሚባክነውም ምግብ ብዙ ነው፡፡ ስለሆነም ሰው ያለውን ሀብት በአግባቡ ሊጠቅም እንዲችል የተለያዩ የግንዛቤ ስራዎች ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን እና ይህም ከቤተሰብ ጀምሮ መሰራት እንዳለበት መክረዋል፡፡ እንደ ሀገር ቤተሰብ ላይ በሚገባ ብንሰራ ያለንንም ሀብት በአግባቡ ብንጠቀም ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ ዕድገትን ማስመዝገብ እንችላለን ሲሉም አክለዋል፡፡
የስነ ልቦና አማካሪ አቶ ማህደር ሳላይህ እንደሚሉት እንደ ሀገር በቤተሰብ ላይ የሰራናቸው ተግባራት በብዙ መልኩ ክፍተት ያሉባቸው ናቸው። በተለይም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ንቁ የሆኑ የቤተሰብ አባላትን በመፍጠር ምቹና ጤናማ ሕይወትን የሚመራ፣ ለሀገር ዕድገት ባለው አቅም ልክ የሚተጋ ትውልድን ከመፍጠር አንፃር የበለጠ መስራት ይኖርብናል። በሌላ በኩልም በአብዛኛው የገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል የተመጣጠነ ምግብ፣ ልብስና መኖሪያ የማገኘት ዕድል እንኳን ቢኖረው ባለው ሀብት ልክ ያለመኖር ክፍተት ይታያል። ይህ ደግሞ ከግንዛቤ ክፍተት የሚመጣ ነው፡፡
የገጠሩ ማህበረሰብ በጓሮው የተለያዩ ልማቶችን ማከናወን እንደሚችል በሚገባ የመረዳትና በዚያው ልክ የመስራትም ክፍተት ይስተዋላል። ስለሆነም የገጠር ኮሪደርን በመሳሰሉ ልማቶች በቤተሰብ ላይ በሁሉም ዘርፍ በመስራት ለለውጥ የሚተጋ ማህበረሰብን መፍጠር እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡
የገጠር ኮሪደር ስራ በገጠር እና በከተማ መካከል ያለውን ሰፊ የአኗኗር ዘዬ ልዩነት በማጥበብ ማህበረሰቦች በቀላሉ የሚገናኙበትን ዕድል ስለሚፈጥር ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል፣ በተሻለ የመጓጓዣ እና የግንኙነት መሠረተ ልማት፣ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ይበልጥ ተደራሽ ይሆናሉ።
የገጠር ኮሪደር ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ እና የስራ ፈጠራን በማጎልበት የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን እንደሚያነቃቁም ምሁራን ይናገራሉ፡፡ የተሻሻለ ተደራሽነት አዳዲስ ንግዶችን መመስረት፣ የስራ እድል መፍጠር እና የሀገር ውስጥ ገቢ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
ገጠር አካባቢዎች እየዘመኑ እና እየበለጸጉ ሲሄዱ፣ የአኗኗር ዘይቤያቸው ይቀየራሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የተሻለ ሀብትን የሚያፈሩበት ዕድል ይፈጠራል፤ ነዋሪዎች በተሻለ የመኖሪያ ቤት እንዲኖሩ ያደርጋል፤ በትምህርት፣ በጤና እና መሰል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይህም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማረጋገጡም በላይ ሁለንተናዊ ደህንነቱ የተረጋገጠ ማህበረሰብንም ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡
በፒተር ዴቪስ እና ኤም.ኤች.አር የተፃፈው “Rural Development: Theory and Practice” በተሰኘው መፅሐፍ ላይ እንደተገለፀው የገጠር ኮሪደር ልማት የገጠሩን ማህበረሰብ ሕይወት በተሻለ መልኩ ለመቀየር ጉልህ አበርክቶ አለው፡፡ ይህንንም መንገድ በከመተል በርካታ ሀገራት እንደ ሀገር ተለውጠውበታል፡፡
ለአብነትም ህንድ የተጠቀሰች ሲሆን ሀገሪቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ “የህንድ ብሔራዊ የገጠር ኑሮ ተልእኮ (ኤን.አር.ኤል.ኤም)” በሚል ተነሳሽነት በገጠሩ ክፍል የግንኙነት እና የገበያ፣ የትምህርት እና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነትን የሚያሻሽሉ ስራዎችን አከናውናለች፡፡ መንደሮችን ከከተማ ማዕከላት ጋር በማገናኘት፣ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት፣ በቤተሰብ ደረጃ ያለውን ሀብት በሚገባ የሚጠቀም ማህበረሰብን ለመፍጠር ባከናወነቻቸው ሰፋፊ ተግባራት ህንድ ትልቅ ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት እንደቻለች በመፅሐፉ ተጠቅሷል፡፡
በቤተሰብ ላይ በመስራት ሌላዋ ተጠቃሽ ሀገር ቻይና ስትሆን በተለይም በገጠር የኮሪደር ስራ የገጠር ክልሎችን ከከተማ ገበያ በማገናኘት፣ የኢንተርኔት ግንኙነትን በማመቻቸት፣ ምቹ የትምህርት እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች እንዲገናኙ በማድረግ እና በቤተሰብ ደረጃ ያላቸውን ሀብት በሚገባ እንዲያውቁ፣ በዚያው ልክም እንዲሰሩና እንዲኖሩ በማድረግ እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግናዋን ማረጋገት እንደቻለችም ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ብራዚልም፣ “ዘላቂ የገጠር ልማት” በሚል መርሃ ግብር ግብርናን የሚያበረታቱ እና የአካባቢን ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ የገጠር ኮሪደሮችን በማልማት ሰርታለች፡፡ ለአብነትም እንደ መንገድና ኮሙዩኒኬሽን ባሉ መሰረተ ልማቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ መንግስት የገጠሩን የገበያ ተደራሽነት አሻሽሏል። ከመንግስት ድጋፍ ባሻገር እንደ ‘ቦልሳ ፋሚሊያ ፕሮግራም’ ያሉ ተቋማት ለዚህ ስራ ስኬታማነት የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣሉ፤ ለድህነት ቅነሳ እና ለገጠር ማህበረሰቦች የተሻሻሉ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶችን ያቀርባሉ፡፡ ይህም በቤተሰብ ደረጃ በኢኮኖሚም ሆነ በማህበረሰባዊ ለውጥ የተሻለ እምርታን ማስመዝገብ እንዳስቻላት ተመላክቷል፡፡
ቤተሰብ ላይ በመስራት በተለይም የገጠሩን የማህበረሰብ ክፍል በሚገባ በመለወጥ ሀገራዊ ብልፅግናዋን ዳር ካደረሱ ሀገራት መካከል ትልቅ ስፍራ እንዳላት የምትጠቀሰው ሌላዋ ሀገር ጃፓን እንደሆነች በመፅሐፉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በተለይም ቤተሰብን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት በመስጠት ዜጎች ገቢያቸውንም ሆነ ቁጠባቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ ስራ ማከናወኗም ተጠቅሷል፡፡
ታድያ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከአነጋገራቸው ምሁራን አስተያየቶች እና ከሀገራት ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያ የጀመረችው የገጠር ኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ አኗኗርን ከመፍጠር ባሻገር የሀገሪቷን ዕድገትም በከፍተኛ መጠን የሚያገዝ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በመለሰ ተሰጋ