በትግራይ ክልል በምርት ዘመኑ ከለማው የሰብል ምርት ግማሽ ያህሉ ተሰበሰበ

AMN- ህዳር 5/2017 ዓ.ም

በትግራይ ክልል በ2016/2017 የምርት ዘመን ከለማው 727 ሺህ ሄክታር መሬት የሰብል ምርት ውስጥ ግማሽ ያህሉ መሰብሰቡን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ከደነው እንደተናገሩት፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ቀድሞ የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት ለመሰብሰብ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ የማስተባበር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የምርት ብክነት ለመከላከል እና የተገኘውን ምርት በአግባቡ ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ 10 ሚሊዮን ብር በመመደብ ለአጨዳ ዘመቻ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን የማሟላት ስራ ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በአጨዳ ዘመቻው ላይ የፀጥታ ሃይሎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የትምህርት ማህበረሰብን ጨምሮ ከ40 ሺህ በላይ የሰው ሀይል እየተሳተፈ መሆኑን አመልክተዋል።

በተደረገው ርብርብም ከክልሉ ምርት እስካሁን 50 በመቶ መሰብሰቡን ያስታወቁት የቢሮው ምክትል ሃላፊ፤ “ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እስካሁን ጉዳት አላደረሰም፣ በቀጣይም ጉዳት እንዳያደርስ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ብለዋል።

የፀጥታ ሃይሎች፣ የመንግስት የስራ ተቋማት ሰራተኞች እና ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች የምርት ብክነት እንዳያጋጥም ከጫፍ እስከ ጫፍ አርሶ አደሩን ለማገዝ በተግባር እያሳዩት ላለው ማመስገናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review