
AMN – ኅዳር 10/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባን ለማዘመን እና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ የተከናወነው ሥራ የሚያስመሰግን መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
የምክር ቤት አባላቱ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ።
በጉባኤው ላይ አስተያየት የሰጡት የምክር ቤቱ አባላት በኮሪደር ልማት እና በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ውብ፣ ለነዋሪዎች ምቹ እና እንደ ስሟ አበባ ለማድረግ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን አንሥተዋል።
በተለይም አዲስ አበባ ከ123 የዓለም ከተሞች እና ከ72 ሀገራት ጋር ተወዳድራ በስማርት ሲቲ ሊደርሺፕ እውቅና ማግኘቷን በመልካም ጎኑ ጠቅሰዋል።
በከተማዋ ሰላምን ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ መሠራቱ አዲስ አበባ የሰላም ከተማ እንድትሆን ማስቻሉን አስረድተዋል።
በተለያዩ ተቋማት የሥራ አካባቢን ለሥራ ምቹ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት መልካም እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም አውስተዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል የኦን ላይን አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ሥራ ጥሩ መሆኑን እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና ገበያን ለማረጋጋት እየተሠራ ያለው ሥራ የከተማ አስተዳደሩን የሚያስመሰግን መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም የተለያዩ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት እንዲሁም የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማደራጀት የሸቀጦችን ዋጋ ለመቀነስ ማስቻሉን አስረድተዋል።
በተለይም የቅዳሜ እና የእሑድ ገበያዎችን የተሻለ የምርት ጥራት እና የሸቀጦች ዋጋ ቅናሽ እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል።
በገበያዎቹ የዋጋ ተመንን በማውጣት ኅብረተሰቡ ጋ ተደራሽ እንዲሆን መደረጉም ጥሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ሴት የመንግሥት ሠራኞች በተቋሞቻቸው የሕፃናት መንከባከቢያ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ በጥራት ማጠናቀቅ፣ በተማሪዎች ምገባ፣ በከተማ ግብርና በኩል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትም እንደ አንደኛው ዙር በተሻለ ፍጥነት እና ጥራት እንዲከናወንም ጠይቀዋል። በኮሪደር ልማቱ በተለይም የአመራር ቁርጠኝነት እና ጥንካሬ የሚደነቅ እንደሆነም አስረድተዋል።
ይሁንና አሁንም በመንገድ እና መሠረተ ልማት (በአዲስ ከተማ ከመሳለሚያ እስከ 18) ተጠናቆ ወደ ሥራ አለመግባት እንደ ችግር ተነሥቷል።
ለአርሶ አደሮች በተሻሻለው መመሪያ መሠረት የካሳ ክፍያ አለመኖር፣ የመሥሪያ ቦታዎች ግናባታቸው ተጠናቅቆ ለተጠቃሚዎች አለመተላለፍ፣ ሰነድ አልባ ቤቶች ላይ ውሳኔ አለመስጠት፣ የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት (አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 እና 2) ተገንብተው ወደ ሥራ አለመግባት እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን አንሥተዋል።
በሰለሞን በቀለ