በነገ ትልም ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ሀገራዊ ህልሞች በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እንዲሆኑ መስራት ይገባል፡-አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር

AMN – ኅዳር 12/2017 ዓ.ም

በነገ ትልም ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ሀገራዊ ህልሞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር ተናገሩ።

19ኛው የብሄሮች ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤትም ቀኑን በፓናል ውይይትና የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህልና ማንነትን የሚያሳይ የባህል ፌስቲቫል በማዘጋጀት እያከበረ ነው።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድርን ጨምሮ የክፍለ ከተማው አመራሮችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ቀኑ በከተማዋ ሲከበር በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠርን አላማ አድርጎ እየተከበረ መሆኑን የተናገሩት አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር ብዝሀነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ብዝሃ ማንነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት አፈጉባኤዋ በዚህም ከተማዋን መቀየር ተችሏል ብለዋል ።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ መኩሪያ ጉርሙ በልዩነት ውስጥ አንድነትን በመገንባት ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

ሀገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ የጽንፈኝነት አስተሳሰብን በማስወገድ ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን መገንባትም የትውልዱ ሀላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ የሚገኘው 19ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ማጠቃለያ ህዳር 29 ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ፍጻሜውን ያገኛል።

በፍቃዱ መለሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review